አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሐምሌ 6፣ 2013 ― በሕግ አግባብና በፍትሕ መንገድ ላይ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ ለመውጣት ሲጣጣሩ ነበሩ የተባሉ ስብሐት ነጋን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት አባላት ላይ በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋዬ አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ለመንግሥታዊወ ልሳን አዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ እነዚህ 42 ተጠርጣሪ የሕወሓት አባላት በቀዳሚ ምርመራና በዋና ምርመራቸው ወቅት ጉዳያቸውን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡
የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር የፍርድ ሂደቱ ዘገየ ለማስባል መሞከራቸውን ያመለከቱት አቶ ፈቃዱ፣ በሕግ አግባብና በፍትሕ መንገድ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ እንወጣለን በሚል ሒሳቦችን ሰርተው ከእስር ለመውጣትም ሲጣጣሩ ቆይተዋል ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡
ነገር ግን ምርመራው በጣም ከታሰበው በላይ በፍጥነት በመጠናቀቁ ይህ ስሌታቸው እንዳልሰራ አመልክተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሰሩት ልክ ሕግ ተገቢውን ፍርድ ይሰጣቸዋል ያሉት አቶ ፈቃዱ፤ በቀጣዩ ሳምንት ተጠርጣሪዎቹ ለክስ እንደሚቀርቡ ያመለከቱ ሲሆን፣ ክሱ የወንጀል ክስ በመሆኑም ፍጥነቱ ምን ያህል ተቀናጅቶ እንደተሰራበት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡