Monday, October 14, 2024
spot_img

ከምርጫው ጋር በተያያዘ ከ200 በላይ ሰዎች ክስ ተመሠረተባቸው

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 5፣ 2013 ― በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድኅረ ምርጫ ወቅት ተፈጸመ በተባለ ወንጀል በአጠቃላይ በአገሪቱ ከኹለት መቶ በላይ ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

በምርጫ አዋጁ 1162/2011 ወይንም በወንጀል ሕግ የተደነገጉ ሥርአቶችን ተላልፈው የተገኙ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን ተናግረዋል።

በዚህም ረገድ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ እና ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በጋራ ሲሠራበት መቆየቱን ኃላፊው አንስተዋል። በተለይም በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ መሥተዳድርን ጨምሮ በአስራ አንድ ምድብ ጽህፈት ቤቶች ያሉ ዐቃቤያን ሕጎች ከምርጫ ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ሲከታተሉ ቆይተዋል ብለዋል።

ሰኔ 14፣ 2013 በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ በአገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች ላይ መጠነኛ አለመረጋጋት ተፈጥሮ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ በጊዜያዊነት ከ200 በላይ ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን የተናገሩት አወል፣ የተፈጸሙትን የወንጀል ድርጊቶች በሦስት ከፋፍለው አስቀምጠዋል።

በአንደኛ ምድብ ምርጫውን ተከትሎ በአገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች ላይ የሰው ህይወት በማጥፋት ወንጀል የተከሰሱ እንዳሉ ገልጸዋል። እንደ ምሳሌም በአማራ ክልል ከምርጫው ጋር ተያይዞ በተፈጠረው አለመረጋጋት አንድ የፖሊስ አባል መገደሉን አንስተው ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ የተከሰሱት ደግሞ የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ ምርጫ በሚካሄድባቸው አከባቢዎች ላይ ኹከት እና ረብሻ የፈጠሩ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ ያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጡት በአጠቃላይ ይሄ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ክስ ከተመሰረተባቸው ከኹለት መቶ በላይ ሰዎች መካከል ሰማኒያ በመቶ የሚሆኑት የሚመለከት ሲሆን፣ እነዚህም ፖስተሮችን የቀደዱ፣ ማስታወቂያዎችን ያበላሹና እንዳያገለግሉ ያደረጉ ሰዎች ናቸው።

በሌላ በኩል በአራተኛነት በክሱ የተካተቱት፣ ምርጫ ሊካሄድ አራት ቀን ሲቀረው ምንም አይነት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ክልክል ነው የሚለውን ሕግ በመተላለፍ ከምርጫው ቀን በፊት እና በምርጫው ዕለት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸውን የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው ተናግረዋል።

ኃላፊው እንደገለጹት፣ ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ምርመራ በማድረግ በቂ ማስረጃ በቀረበባቸው ሰዎች ላይ ክስ መስርቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img