Sunday, September 22, 2024
spot_img

‹‹እነ ጃዋር ይፈቱ›› ያለው መሐመድ ዴክሲሶ በዶሮ እርባታ ሥፍራ ታስሮ መቆየቱን ገለጸ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 5፣ 2013 ― የጂማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ‹‹እነ አቶ ጃዋር መሐመድና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ›› በሚል ባስተጋባው መልዕክት ለወራት ያህል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የቆየው መሐመድ ዴክሲሶ፣ የመጨረሻ የእስር ቆይታው በአዋሽ መልካሳ የዶሮ እርባታ ሥፍራ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጧል፡፡

መሐመድ በአዋሽ መልካሳ የዶሮ እርባታ ከአንድ ወር ተኩል በላይ በእስር መቆየቱንና ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እሱን ጨምሮ በርካቶች ሲለቀቁ፣ አሁንም ሌሎች በዶሮ እርባታው ሥፍራ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡

የጂማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ የነበረው መሐመድ በታሰረባቸው ባለፉት አምስት ወራት፣ ከዶሮ እርባታው ሥፍራ ቀድሞ አምስት ወይም ስድስት የእስር ቦታዎች መቆየቱንም አመልክቷል፡፡

መሐመድ እንደሚለው ከነዚህ ቦታዎች ውስጥ ‹‹ሁለቱ ብቻ መደበኛ ማቆያ ነበሩ፣ ቀሪዎቹ ሕገ ወጥ የማሰቃያ ቦታዎች ናቸው›› ሲል ተናግሯል።

መሐመድ አክሎም በቆየበት የዶሮ ማርቢያ ቦታ ስለነበረው አያያዝም ‹‹የዶሮ ማርቢያ ሲባል ‹‹ያው የሚታወቅ ነው፣ የሚመች አያያዝ አልነበረም›› በማለት አስረድቷል።

በጂማ ዩኒቨርሲቲ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፈው መልዕክት ቁጭት እንደሌለበት የገለጸው መሐመድ፣ ‹‹ማንም ማወቅ ያለበት ነገር የመብት ጥያቄ ስለሆነ ያነሳሁት፤ የሚያሳስበኝ ወይም የሚያስፈራኝ ነገር የለም›› ብሏል።

መሐመድ ታስሮ የቆየባቸው ቦታዎችን በተመለከተ መንግሥትም ሆነ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ያለፉትን በርካታ ወራት በእስር ላይ ያሳለፈው መሐመድ ዴክሲሶ፣ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሐምሌ 3፣ 2013 ጧት አካባቢ መፈታቱንና እና ከቤተሰቦቹ ጋር ከቀኑ ሰባት ሰዓት መገናኘቱን አስረድቷል።

መሐመድ ዴክሲሶ ‹‹እነ ጃዋር መሐመድ ይፈቱ›› የሚል መልእክት ባስተጋባበት የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መድረክ ላይ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት ታድመው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img