Friday, November 22, 2024
spot_img

በእስር ላይ በሚገኙ ጋዜጠኞች ላይ የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በአፋጣኝ ሊለቀቁ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሐምሌ 4፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በእስር ላይ የሚገኙ የኢትዮ ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝ ሕግን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባና የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል ብሏል።

ኮሚሽኑ ሰኔ 23፣ 24 እና 25 2013 በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር የሚገኙትን በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ አበበ ባዩ፣ መልካም ፍሬ ይማም፣ ፍቅርተ የኑስ፣ ዊንታና በርሄ እና ምህረት ገብረክርስቶስን ጨምሮ 21 የኢትዮፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርበት ሲከታተል መቆየቱንም አመልክቷል።

ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል ሦስቱን እና አንድ ሌላ ታሳሪን ጨምሮ አራት እስረኞች ማክሰኞ ሰኔ 29፣ 2013 አመሻሽ ላይ መለቀቃቸውንና ቀሪዎቹ ታሳሪዎች በወንጀል ስለተጠረጠሩ ለምርመራ ስራ በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ መሰጠቱን ፖሊስ የገለጸ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ እስከ ሐምሌ 3፣ 2013 ምሽት ድረስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማየቱና ታሳሪዎቹን ለመጎብኘት አለመቻሉ፤ እንዲሁም ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ሳይገናኙ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸው ኮሚሽኑ እጅግ የሚሳስበው መሆኑን አመልክቷል።

የማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑና በእስር ያሉ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብት ፈጽሞ ሊከለከሉ የማይገቡና፤ ተጠርጣሪዎች በሕይወት መኖራቸውንና አካላዊ ደኅንነታቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሰረታዊ የሕግ ጥበቃዎች መሆኑንም አስታውሷል።

ስለሆነም የፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አሁንም በእስር ያሉ የአውሎ ሚድያና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞችና ሰራተኞች በሙሉ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው እንዲገናኙ እንዲያደርጉ፣ የታሳሪዎቹን የእስር ሁኔታ ሕጋዊነት እንዲያስረዱና፣ ከፍርድ ቤት የተሰጠ የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በስተቀር ታሳሪዎቹ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳስቧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ሕግን ያልተከተለ ማንኛውም አይነት እስር በሕግና ፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚኖርን እምነት የሚሸረሽር በመሆኑ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር ሙሉ በሙሉ መቆም ያለበት ተግባር መሆኑን ገልጸው “ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹን ለመጎብኘትና የአያያዛቸውን ሁኔታ ለማወቅ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል” ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img