አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሐምሌ 3፣ 2013 ― መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የተዛቡ መግለጫዎች ከመስጠት እንዲቆጠብ ጠይቋል፡፡
መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮው በትግራይ ሁኔታ የተዛቡ መግለጫዎች ሲያወጣ ነበር፡፡
ቢሮው የሚያከናውናቸውን ገንቢ ያልሆኑ ተግባራት ኢትዮጵያ ከተቋሙ ጋር በፈረንጆቹ ከ1984 አንስቶ የገነባቸውን ግንኙነት የሚሸረሽር በመሆኑ፣ ድርጊቱን በመቃወም ለተመድ ዋና ጸሐፊ ደብዳቤ መፃፉንም አመልክቷል፡፡
የትግራይን ሁኔታ በተመለከተ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ፣ ‹‹ቢሮው የነበረው ሚና እና የሚያወጣቸው የተዛቡ ሪፖርቶች ገንቢ አልነበሩም›› ብሎ እንደሚያምን መንግስት አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሪፖርቶች የህወሐትን የተሳሳተ አስተሳሰብን የሚያጠናክር፣ የሚበራታታ እና ለማወደስ የተቀየሰ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በክልሉ ያለውን ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳ የሚያደርግ ይመስላልም ብሎታል፡፡
‹‹ቢሮው ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጀውን ህገ-ወጥ ቡድን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት እያለ የሚጠራ ተቋም ነው›› ያለው መንግስት፣ ከመሰል ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንዲሁም ለተቋሙ እና ኢትዮጵያ የቆየ ግንኙነት ሲባል የእርምት እርምጃዎች እንዲወስድ ሲልም ጠይቋል፡፡
መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁምን ካወጀበት አንስቶ ከሰብዓዊ ስራዎች ጋር በተያያዘ በቅርበት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲያረጋግጥ መቆየቱንም ማስገንዘቡን የዘገበው አል ዓይን ነው፡፡