Sunday, July 7, 2024
spot_img

ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ዶክተር ስለሺ በቀለ ውዳሴ እየቸሩ ይገኛሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 2፣ 2013 ― የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲነሳ በቀዳሚነት ሥማቸው ከሚጠቀሱ ሰዎች መካከል አንዱ ለሆኑት የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውዳሴ እየቸሩ ይገኛሉ፡፡

ለዶክተር ስለሺ በቀለ የሚቀርበው ውዳሴ የመጣው ትላንት ምሽት በተደረገው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለአገራቸው ወግነው ያቀረቡትን ንግግር ተከትሎ ነው፡፡

ሚኒስተሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ በአዲስ አበባ፣ ካርቱም፣ ካይሮ፣ ዋሽንግተን፣ ኮንጎ ኪንሻሳ፣ ኒው ዮርክ እና በሌሎችም ስፍራዎች ሲካሄዱ በቆዩት ድርድሮች ላይ ኢትዮጵያ ወክለው የተደራደሩ ናቸው፡፡

ዶክተሩ የሕዳሴው ግድብ ድርድር ከስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ውሃ ሙሌት መከናወን የለበትም በሚል ሱዳንና ግብጽ አጥብቀው ቢከራከሩም፣ ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰ ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ መሙላቷን አታቆምም በማለት የአገራቸውን ቁርጥ ያለ አቋም በተደጋጋሚ ግልጽ አድርገዋል።

ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ዶክተር ስለሺ በቀለ፣ በአሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥራቸውን ለቀው አገራቸውን ለማገልገል የመጡት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በቀረበላቸው እንደነበር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዶክተር ስለሺ በቀለ በአሁኑ ወቅት ካሉበት የሚኒስትርነት ቦታ በፊት ኒውዮርክ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ የማኅበራዊ ጉዳዮች ክፍል የኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ላይ ክልላዊ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግሥታትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉት አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መስራት በጀመሩበት ወቅት ሲሆን፣ በጊዜው የውሃና የአየር ጸባይ ለውጥ ባለሙያ ሆነው ነበር የሚሰሩት።

በተባበሩት መንግሥታት በነበራቸው ቆይታ ዶክተር ስለሺ ዘላቂ ልማት ከብሔራዊ የእድገት እቅዶች ጋር መጣመር የሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገርላቸዋል።

በዚህም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አባል በሆኑ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን አካባቢ በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻሉ ባለሙያ ናቸው።

በመጀመሪያዎቹ የሥራ ኃላፊነታቸው ደግሞ ዶክተር ስለሺ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ዲን ሆነው አገልግለዋል።

በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ኃላፊነትም ግድብና ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ መስኖ እና የውሃ ፍሰት እንዲሁም የውሃ ሀብት እና የሀይድሮሎጂ ዲፓርትመንቶችን አቋቁመዋል። በተጨማሪም ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ ሀብት፣ የውሃ አጠቃቀምና አስተዳደር እንዲሁም የከባቢ አየር ተጽእኖን የተመለከቱ ኮርሶችን ኢትዮጵያ እና ጀርመን ውስጥ አስተምረዋል።

ዶክተር ስለሺ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ያገኙ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውካስል በሃይድሮሊክ ኢንጂኒየሪንግ እና ሃይድሮሎጂ ሰርተዋል።

ዶክተር ስለሺ በውሃ ሀብትና እና ሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከድሬስደን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ ማግኘት ችለዋል።

ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ባልደረቦች በነበሩበት ጊዜ ባዳበሩት ትውውቅና በዘርፉ ባላቸው ጥልቅ ዕውቀት ሳቢያ አገራቸውን በሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ ሲጠየቁ ያለማቅማማት ነበር የተቀበሉት።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img