Sunday, September 22, 2024
spot_img

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎች መነሻቸው አዲስ አበባ እንደሚሆን አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 2፣ 2013 ― የሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አምባሳደሩ ለትግራይ ክልል ለሚደረገው የሰብአዊ እርዳታ የዓለም አቀፍ ተቋማት የበረራ ፍቃድ ቢሰጥም፤ እያንዳንዱ በረራ ግን መነሻው ከአዲስ አበባ እንደሆነ ገልፀዋል።

ለሰብዓዊ እርዳታ በሚል ወደትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስረድተዋል።

እያንዳንዱ በረራ አዲስ አበባ ካለፈ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል እንደሚሄድ እና ሲመለሱም አዲስ አበባ አርፈው መሄድ እንደሚጠበቅባቸው ማስገንዘባቸውን አል ዓይን ዘግቧል፡፡

ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‹‹አንፈተሽም ያለ ካለ ባይመጣ ይሻላል›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል አምባሳደሩ የትላንትናው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የልማት እና አፍሪካዊ ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጠ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ብለውታል፡፡ በምክር ቤቱ ተለዋጭ እና ቋሚ አባል ሀገራት ጋር በተናጠል የተሰራው የማስረዳት ስራ ፍሬ ማፍራቱን ያሳየ ስብሰባ ነበር ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ንግግራቸው ከኤምባሲዎችና አጠቃላይ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በተመለከተ ያነሱትን ነጥብ ተከትሎ በተለያዩ የትስስር ገፆች ሲራገብ የነበረውን የ‹‹30 ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ሊዘጉ ነው›› ወሬን ከእውነት የራቀ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ዲና ‹‹ተዘጉ የተባሉ ኤምባሲዎች ዝርዝር ጉዳይ ውሸት ነው›› ያሉ ሲሆን፣ የዲፕሎማቶችን ጥሪ በሚመለከት ከሆነ የተለመደ አሰራር መሆኑንና አዲስ ነገር አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደሌሎች ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች ሁሉ፤ የተቋም ሪፎርም እየተደረገ መሆኑንና በሂደት የሚኖሩ ለውጦች ካሉ ይፋ እንደሚደረገም ቃል አቀባዩ ተናግሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img