አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 1፣ 2013 ― ዓለም አቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የትግራይ ክልል ከተሞች በሆኑት በአክሱም፣ አዲግራት እና አቢ አዲ ከተሞች የሕክምና ሥራውን ማቋረጡን ወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተጠቀሱት አካባቢዎች ሥራውን ያቋረጠው ከሁለት ሳምንት በፊት 3 ሠራተኞቹ ስለተገደሉበት መሆኑን የጠቀሰው ቡድኑ፣ የሠራተኞቹ ግድያ በአፋጣኝ እንዲመረመር እና የገዳዮች ማንነት እንዲገለጽለት ጠይቋል፡፡
ለግድያው እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩን እና የአገዳደሉ ሁኔታ እንደተሸፋፈነ መቅረቱን ቡድኑ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሦስት ባልደረቦቹን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገድለው ማግኘቱን የገለጸው ሰኔ 19፣ 2013 እንደነበር ይታወሳል፡፡
የሐኪሞች ቡድኑ ተገደሉብኝ ያላቸው ባልደረቦቹ የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪዋ ማሪያ ሄርናንዴዝ፣ ምክትሏ ዮሐንስ ሐለፎም እና አሽከርካሪው ቴድሮስ ገብረማርያም ናቸው፡፡
የስፔን ዝግነት ያላት የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪዋ፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት በድርጅቱ የቆየች ሲሆን፣ ሁለቱ ኢትዮጵያውን ባለፈው ጥር እና ግንቦት ወር ላይ የድርጅቱ አባል የሆኑ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ግድያውን አስመልክቶ በወቅቱ ለሚዲያዎች የተናገሩት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮለኔል ጌትነት አዳነ፣ በትግራይ ክልል አብይአዲ አካባቢ የ3 ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሰራተኞችን ሕወሃት ከመኪናቸው አስወርዶ እንደገደላቸው አስታውቀዋል፡፡