አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 29፣ 2013 ― ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ሙሌት መጀመሯን እንዳስታወቀች የግብጽ ባለሥልጣናት ይፋ ማድረጋቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የግድቡ ሁለተኛው ዙር ሙሌት መደረጉን የመስኖ እና ውሃ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ለግብጹ አቻቸው መሐመድ ዐብዱል አቲ በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ማሳወቃቸውንም አህራም የተባለው የግብጽ ሚዲያ አረጋግጧል።
ይህንኑ ተከትሎም የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ሳይጀመር በፊት ከስምምነት መደረስ እንዳለበት ውትወታ ሲያደርጉ የሰነበቱት የግብጽ ባለሥልጣናት እና የአገሪቱ ሚዲያዎች በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ምላሾችን እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡
የግብጽ የመስኖ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት መሐመድ ጋኒም በአገሩ የቴሌቪዥን ቻናል ቀርበው አገራቸው የግድቡ ሙሌት ምንም ዐይነት ተጽዕኖ አምጥቶ ማየት እንደማትሻ መናገራቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
በግድቡ ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የፊታችን ሐሙስ ለመነጋጋር ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት በማካሄዷ የግብጹ መስኖ ሚኒስትሩ መሐመድ ዐብዱል አቲይ ኢትዮጵያ የላከችውን ደብዳቤ አያይዘው ለምክር ቤቱ ማሳወቃቸውም ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ተፈጥሮ ያደላትን መብት መጠቀሟን መነገሩን ያመለከተው የዜና ወኪሉ፣ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከኢትዮጵያ ጋር ሲነታረኩ የቆዩት ግብጽ እና ሱዳን ግድቡ እስከ ሦስትና ዓመት ድረስ ያለውን ሒደት በዝርዝር ስለሚያቁት ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ማቅረቡ አስፈላጊ አለመሆኑን መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር በኩል በተያዘው ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘምና ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ስትገልጽ መሰንበቷ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የመጀመር ዜና መውጣቱን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡