Sunday, September 22, 2024
spot_img

በአፋር የሚንቀሳቀሱ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልሉን ገዢ ፓርቲ ወቀሱ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 28፣ 2013 ― አምስቱ የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ የብልጽግና ፓርቲ የአፋር ቅርንጫፍ ‹‹ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ ብሎም ተዓማኒ ነበር’ በማለት ሀሰተኛ መግለጫ አውጥቷል›› ሲሉ ከስሰዋል።

የክልሉ ገዢ ፓርቲ በመግለጫው ‹‹እውነትን፣ ፍትህን እንዲሁም ዲሞክራሲን ለመቅበር ሞክሯል›› ሲሉም ተችተዋል።

መግለጫውን ካወጡት አምስት ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም፤ ‹‹እኛ የተስማማን አስመስለው ነው መግለጫ ያወጡት›› ሲሉ ፓርቲያቸውም ሆኑ ሌሎች ተቃዋሚዎች የመግለጫው አካል እንዳልሆኑ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ‹‹እነሱ ያወጡት [መግለጫ] እኛን የማይወክለን፣ ተቀባይነት የሌለው፣ በምንም አይነት መስፈርት ልንቀበለው የማንችል ነገር ነው›› ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አወዛጋቢው መግለጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አባል በሆኑበት የአፋር ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስም የወጣው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 22፤ 2013 ነበር። ይህ መግለጫ ከመውጣቱ አንድ ቀን አስቀድሞ በአፋር ክልል ዋና ከተማ በሰመራ በተካሄደው የጋራ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ከስምምነት ላይ አለመደረሱን ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ይገልጻሉ።

‹‹እነሱ ያቀረቡት ሀሳብ ‘ምርጫው ፍትሃዊ፣ ተዓማኒ እና ቅቡልነት ያለው ምርጫ ነበር’ የሚል የጋራ መግለጫ እናውጣ ነው›› ሲሉ በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ ያስረዱት አቶ ሙሳ አደም፤ ‹‹ይሄ የሚገልጸን ተግባር ስላልሆነ በዚህ አንስማማም በማለት ነው ከመግለጫው የወጣነው”››ብለዋል።

በአምስቱ ፓርቲዎች መግለጫ ላይም ተመሳሳይ ሀሳብ ተንጸባርቋል። ‹‹ይህ የብልጽግና አፋር ቅርንጫፍ መግለጫ በእኛ በኩል በምንም አይነት መስፈርት ተቀባይነት የሌለው፤ ሀሰተኛ እና መሰረተ ቢስ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን›› ሲሉ ፓርቲዎቹ በመገለጫቸው ላይ አበክረው ገልጸዋል።

‹‹[በምርጫው] በነጻ ተወዳደርን ለማሸነፍም ለመሸነፍም እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞናል›› ያሉት አምስቱ ፓርቲዎች፤ ‹‹በክልላችን ምንም አይነት የምርጫን መስፈርት የሚያሟላ ምርጫ ስላልተደረገ በክልሉ ድጋሚ ምርጫ መደረገ አለበት›› ሲሉ ከዚህ ቀደም ባወጡት መግለጫ ያነሱትን ሀሳብ በድጋሚ አስተጋብተዋል።

በተቃውሞ መግለጫው ላይ ስማቸው የተዘረዘሩ አምስት ፓርቲዎች ቢሆንም፣ ጉዳዩን በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ በተሰጠው መግለጫ ላይ የተገኙት ግን የሦስት ፓርቲ አመራሮች ብቻ ናቸው። የአፋር ህዝብ ፓርቲ እና የአፋር ህዝብ ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በሊቀመንበሮቻቸው አማካኝነት በመግለጫው ላይ ሲሳተፉ፤ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር በበኩሉ ምክትል ሊቀመንበሩን ልኳል።

የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ፓርቲ እና የአርጎባ ብሔረሰብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች በዛሬው መግለጫ ላይ ሳይገኙ መቅረታቸውን የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img