አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 28፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በትግራይ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የሰብአዊ አቅርቦት እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል፡፡
በመንግሥታቱ ድርጅት ድረ ገጽ በተነበበው የዋና ጸሐፊው ቃል፣ በትግራይ ክልል የመሠረተ ልማቶች መፍረሱን ማውገዛቸው ተመላክቷል፡፡
ጉቴሬዝ ይህን ያነሱት ከቀናት በፊት ለትግራይ ክልል የሰብአዊ አቅርቦት ዋንኛው መስመር ነው የሚባለው የተከዜ ድልድይ መፍረሱን ተከትሎ ነው፡፡
ከድልድዩ መፍረስ ጋር በተገናኘ የፌዴራል መንግሥት የሕወሃት ኃይሎችን በአፍራሽነት የወነጀለ ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ቢሮ በበከኩሉ የአማራ ልዩ ኃይል አፍርሶታል የሚል ሪፖርት ደርሶኛል ብሎ ነበር፡፡
በሌላ በኩል አንቶንዮ ጉቴሬዝ በትግራይ ክልል መፍትሔ ለማምጣት ወደ ድርድር የሚመራ እውነተኛ የተኩስ አቁም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የተኩስ አቁሙን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ከሳምንት በፊት ሰኔ 21 የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ በትላንትናው እለት መግለጫ ያመጣው ሕወሃት የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠበትን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ሕወሃት ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የኤርትራ ወታደሮችና እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቅ ይገኝበታል።
በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግባቸው ህወሃት የጠየቀ ሲሆን፣ ቴሌኮምና መብራትን ጨምሮ የተቋረጡ አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩም ጠይቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም “ያለ ቅድመ ሁኔታ ዓለም አቀፍ በረራዎች በትግራይ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች በቀጥታ ጉዞ እንዲያደርጉ መፈቀድ” እንዳለበትም የጠየቀው ሕወሃት፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንዲከበርና ይህም ለሚደረጉ ማናቸውም ድርድሮች ዋነኛ መሠረት እንዲሆን ከመጠየቁ በተጨማሪ የዚህ ዓመት የክልሉ በጀት እንዲለቀቅ፣ ነገር ግን የትኛውም የፌደራሉ መንግሥት ወታደራዊና የጸጥታ ኃይል ወደክልሉ እንዳይገባና እንዳይንቀሳቀሱም ብሏል፡፡