አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 28፣ 2013 ― የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ከትግራይ ክልል ጋር የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውና በቅርቡ በትግራይ በነበረው ጦርነት በአማራ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር የዋሉት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ጉዳይ ፋይሉ የተዘጋ ነው ብለዋል፡፡
ርእሰ መስተዳደሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ‹‹ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያወራርደዉን ሒሳብ ተዘጋጅተን እንጠብቀዋለን›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡
የአቶ አገኘሁ ምላሽ የመጣው ከሰሞኑ የሕወሃት አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለሬውተርስ የዜና ወኪል ኤርትራና አማራ ክልል ድረስ በመግባት ‹‹ጠላት›› ያሏቸውን እንደሚዋጉ መናገራቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ፀለምትና ራያ አማራነት የተረጋገጠ፤ የተዘጋ ፋይል መሆኑን ደግመን ደጋግመን እናረጋግጣለን ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ፣ ‹‹ወልቃይትና ራያ የወያኔ መቀበሪያ እናደርጋቸዋለን›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ የሕወሃት አመራሩን ንግግር ተከትሎ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምት እና ራያ ‹‹በራሳቸው መስዋትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን›› የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡
አክሎም እነዚህን አካባቢዎች ‹‹ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ፣ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌለ መሆኑን›› እናረጋግጣለን ማለቱም አይዘነጋም፡፡