አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሰኔ 27፣ 2013 ― ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለስምንት ወራት የዘለቀ ጦርነት ውስጥ የገባው ህወሓት በክልሉ የተኩስ አቁም መደረጉን በመርኅ ደረጃ እንደሚስማማና ለዚህም ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ ጠይቋል።
ህወሓት ይህንን ያሳወቀው በዛሬው ዕለት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በሚል ባወጣው መግለጫው ነው።
ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከልም በጦርነቱ ውስጥ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰሱት የጎረቤት አገር የኤርትራ ወታደሮችና እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቅ ይገኝበታል።
በተጨማሪም ሕወሃት ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግባቸው ህወሃት የጠየቀ ሲሆን፣ ቴሌኮምና መብራትን ጨምሮ የተቋረጡ አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩም ጠይቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም “ያለ ቅድመ ሁኔታ ዓለም አቀፍ በረራዎች በትግራይ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች በቀጥታ ጉዞ እንዲያደርጉ መፈቀድ” ከቅድመ ሁኔታው ውስጥ አካቷል።
ህወሓት በቅድመ ሁኔታው ውስጥ ያለምንም ገደብ የሰብአዊ እርዳታ የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻችና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቋል።
መግለጫው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንዲከበርና ይህም ለሚደረጉ ማናቸውም ድርድሮች ዋነኛ መሠረት እንዲሆን ከመጠየቁ በተጨማሪ የዚህ ዓመት የክልሉ በጀት እንዲለቀቅ፣ ነገር ግን የትኛውም የፌደራሉ መንግሥት ወታደራዊና የጸጥታ ኃይል ወደክልሉ እንዳይገባና እንዳይንቀሳቀስ የሚልም የቅድመ ሁኔታው አንድ አካል ነው።