አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሰኔ 27፣ 2013 ― ሕወሃት የአገር መከላከያ ሠራዊትን የተናጠል ተኩስ አቁም እና ከመቀሌ መውጣት ተከትሎ በከተማዋ እና በሌሎች የትግራይ ከተሞች በመግባት በክልሉ ነዋሪ ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን እያደረሰ እንደሚገኝ በመንግሥት የሚመራው የአስቸኳይ ገዜ መረጃ ማጣሪያ ገጽ አሳውቋል፡፡
ገጹ በመቀሌ እና በሌሎች ከተሞች ሕወሃት ‹‹ከጊዜያዊ አስተዳሩ እና መከላከያን ተባብራችኋል ያላቸው ንጹሃን ላይ ግድያ እየፈጸመ› ይገኛል ያለ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ተግባሩ የትግራይ ያለውን የሰብዓዊ አቅርቦቶች እጥረት አባብሶ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር የሚያደርግ›› መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ቡድኑ ‹‹መንግስት ያደረገውን ዐይነት የተኩስ አቁም ከማድረግ ይልቅ የኢትዮጵያን እና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በሐሰተኛ የድል ፕሮፓጋንዳዎች ለማታለል እና ትኩረት ለማግኘት በሚያደርገው መፍጨርጨር የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎችንና የዜጎች ደህንነት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እያስገባ እንደሆነ ኢትዮጵያዊያን እና የዓለመ አቀፉ ማኅበረሰብ ሊረዳ ይገባል›› ብሏል፡፡
በተያያዘ መረጃ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት የሆኑት ኮለኔል ጌትነት አዳነ ሕወሃት ከሰሞኑ ማረኳቸው የሚላቸው ወታደሮችን በተመለከተ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ ምላሻቸው ቁጥሩን ባይናገሩም ከአገር መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች መካከል በተለይ መካከለኛ ወታደሮች አንዳንዶች በሕዝብ ላይ አንተኩስም ብለው ራሳቸውን ጭምር የሰዉ እንደነበሩ ያነሱት የሕዝብ ግንኙነቱ፣ ሌሎች የበታች ወታደሮችም ለሕዝብ እጃቸውን መስጠታቸውን ተናግረው ሕወሃት ማርኬያለሁ ማለቱን ‹‹በረሐ እየተዋጋሁ ከርሜያለሁ ለማለትና ሕዝቡን ማታለያ ነው›› ብለውታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ የተመለሰው ሕወሃት፣ ከአመራሮቹ መካከል በሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በኩል፣ 6 ሺሕ ወታደሮች ማርኬያለሁ ማለቱን የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ማስነበቡ መነገሩ አይዘነጋም፡፡