አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 26፣ 2013 ― ከሰሞኑ ዳግም የትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለን መቆጣጠራቸው የተነገረው የሕወሃት ኃይሎች፣ 6 ሺሕ ያክል የአገር መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች መማረካቸውን ከአመራሮቹ መካከል የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ነግረውኛል ብሎ ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል፡፡
ወታደሮቹን አስመልክቶ በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ጋር እየተነገገሩ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን፣ በቅርቡ የበታች ወታደሮችን እንደሚለቁና በመሪነት ደረጃ ላይ ያሉትን ግን በቁጥጥራቸው ስር እንደሚያቆዩ ጠቁመዋል ነው የተባለው፡፡
ዶክተር ደብረጽዮን ማርከናቸዋል ያሏቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች፣ በሰልፍ ሆነው በመቐለ ጎዳናዎች ላይ ሲጓዙ የሚያሳዮ ፎቶዎችን ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው አያይዟል፡፡
እነዚሁ በዘገባው ተዳክመው መቀለ ደርሰዋል የተባሉት የአገር መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች፣ ወንዶቹ ከሴቶች ለየብቻ ተለይተው ወደ ማረሚያ ቤት መግባታቸው ነው የተነገረው፡፡
ሕወሃት ማርኬያቸዋለሁ ያላቸውን እነዚህን ወታደሮች በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከፌዴራል መንግሥት በኩል የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡