አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 26፣ 2013 ― ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለፉትን ስምንት ወራት በጦርነት ያሳለፈው የሕወሃት አመራሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ የራሳችንን እድል በራሳችን እንድንወስን የሚደረገውን ሁሉንም እናደርጋለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ዶክተር ደብረጽዮን ይህን ያሉት የሕወሃት ኃይል መቐለን ከተቆጣጠረ በኋላ አደባባይ ወጥተው ባደረጉት ንግግር ላይ መሆኑን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል፡፡
የሕወሃት አመራሩ በንግግራቸው ‹‹በሕዝብ የተመረጠ ሕዝባዊ መንግሥት ወደ ቦታው ተመልሷል››፣ ሆኖም የትግራይ ሕዝብ ግን ‹‹ጉልበትም አስፈላጊ በመሆኑ›› የታጠቀውን እንዳይፈታ ማሳሰባቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሕወሃት መቐሌን እስከሚለቅ ድረስ ሕወሃትን በሊቀመንበርነት የመሩት ደብረጽዮን፣ ‹‹ሕልውናችንን ለማረጋገጥ፤ የራሳችንን እድል በራሳችን እንድንወስን ሁሉንም የሚደረገውን እናደርጋለን›› ማለታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
አክለውም ‹‹አሁንም ፍላጎታችን ሰላምና ልማት ነው›› ነገር ግን ‹‹በሕዘብ ላይ በደል የፈጸሙ እንዲጠየቁ እንሠራለን›› ማለታቸውም ተነግሯል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት መቐለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የሕወሃት ኃይሎች ሰኞ ሰኔ 21 የትግራይ ክልል መቀመጫ መቀለን መቆጣጠራቸው መነገሩ ይታወሳል።