Friday, November 22, 2024
spot_img

የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ በዛሬው እለት ይመክራል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 25፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ሁኔታ ላይ ለመምከር ስብሰባ መጥራቱ ተሰምቷል፡፡

ይህ ስብሰባ በ8 ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በግልጽ የሚመክር የመጀመርያው ሸንጎ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

ስብሰባውን አስመልክቶ ቢቢሲ ‹‹ኒውስዴይ›› በተባለው የራድዮ መርሐ ግብር አናገርኳቸው ያላቸው በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ መነጋገራቸው እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለውኛል ሲል ዘግቧል፡፡

አምባሳደር ሊንዳ ‹‹በዚህ ጦርነት ውስጥ እጃቸው ያለበት አካላት ማወቅ ያለባቸው፣ የጸጥታው ምክር ቤት አሁኑኑ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ማየት እንደሚሻ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በረሐብ አፋፍ ላይ ናቸው ያሉት አምባሳደሯ፣ ይህ ደግሞ ረሐብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም ነው ሲሉ መክሰሳቸውንም ዘገባው አመለክቷል፡፡

‹‹ሁላችንም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ እንደሆነ በጽኑ እናምናለን፡፡ ልዩነት ያለን እንዴት ጉዳዩ ይፈታ በሚለው አካሄድ ላይ ነው›› ያሉት አምባሳደር ሊንዳ ግሪንፊልድ ዞሮ ዞሮ ‹‹የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አንዳች ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለበት በሁላችንም የሚታመን ነው፤ አያጠራጥርም›› ሲሉም አክዋለዋል ብሏል – ቢቢሲ በዘገባው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት አሉት፡፡ ከ15ቱ አባል አገራት አምስቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ሲሆኑ፤ አስሩ ደግሞ በየዓመቱ የሚቀያየሩ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም የሌላቸው አባል አገራት ናቸው። ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img