አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 25፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቀጣይ ሳምንት በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሊመክር እንደሚችል ሬውተርስ በመንግሥታቱ ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላ ዲቭጌ ተናግረዋል ሲል ዘግቧል፡፡
የፈረንሳዩ ተወካይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከሆነ የጸጥታው ምክር ቤት አገራቱን ከስመምምነት እንደዲደርሱ ዳግም ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ከማድረግ የዘለlለ የሚያደርገው ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደሉም፡፡
የግድቡን ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መውሰድ በተመለከተ ከሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪዎች መካከል የሆነችው ሱዳን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በተከሰተው አለመግባባት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃ ነበር፡፡
ሱዳን በጽሐፍ ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ ‹‹በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ደኅንነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል›› ባለችው ግድብ ጉዳይ እንዲወያይ ነበር ያመለከተችው፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መርያም አል መሕዲ አማካይነት ለጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊ በተጻፈው ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ ‹‹በተናጠል›› ግድቡን በውሃ ከመሙላት እንድትታቀብ እንዲጠይቁም ሐሳብ ሰንዝረዋል።
በተመሳሳይ የዐረብ ሊግ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት በሕዳሴ ግድብ ላይ ተገናኝተው እንዲመክሩ መጠየቁም ይታወሳል፡፡
ሆኖም የዐረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ በኳታር ተወያይቶ ያሳለፈውን ይህንኑ ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል መንግስት መኮነኑ አይዘነጋም፡፡
የኢተዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በግድቡ ጉዳይ ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጪ የሚደረግን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበልና በቀጣይ ወር ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም በተያለት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን ደጋግሞ ሲያሳውቅም መሰንበቱም ይታወቃል፡፡