– የተመድ ድልድዩ የፈረሰው በአማራ ልዩ ኃይል መሆኑን ሪፖርት አውጥቷል
አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 25፣ 2013 ― በትላንትናው እለት መፍረሱ የተነገረው የተከዜ ድልድይ አፍራሹ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሃት መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ባወጣው አጭር መግለጫ አስታውቋል፡፡
ማጣሪያው ባወጣው መግለጫ ‹‹የትግራይ አርሶ አደሮች የመኸር ግብርና እንዲያከናውኑ ለመደገፍ የወጣውን የሰብአዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ውድቅ ያደረገው የሽብር ቡድኑ ህወሃት የተከዜ ድልድይን ሆን ብሎ ወደ ክልሉ የሚወስደውን የእርዳታ መስመር ለመገደብ አውድሟል›› ብሏል፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ባወጣው ወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ ሪፖርቱ በትላናትናው እለት የተከዜ ድልድ የፈረሰው በአማራ ልዩ ኃይል ነው ብሏል፡፡
ቢሮው በሪፖርቱ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ሰኔ 22፣ 2013 በአሁኑ ወቅት በአማራ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር የሚገኙ በትግራይ ክልል ካርታ ሥር የሚገኙ አካባቢዎችን አናስነካም ማለታቸውን ያስታወሰ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎም ድልድዩ በልዩ ኃይሉ እንደፈረሰ ነው የገለጸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ያወጣውን ሪፖርት በተመለከተ ከፌዴራል መንግሥትም ሆነ ከአማራ ክልል በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡
በሌላ በኩል የመንግሥታቱ ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን ያሳወቀ ሲሆን፣ ጥቂት የተራድኦ ተቋማት በመቐለ፣ ሽረ እና ማይ ጸብሪ አካባቢዎች በሳተላይት መገናኛዎች እንደሚጠቀሙ፣ በአፋር በኩልም ሆነ በአማራ ክልል በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሚያስገቡ መንገዶች መዘጋታቸውን እንዲሁም በክልሉ የጥሬ ብር እና የነዳጃ እጥረት በመኖሩ የረድኤት ሠራተኞች እንቅስቃሴ ላይ እክል እንደፈጠረ አሳውቋል፡፡