Saturday, November 23, 2024
spot_img

በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች እስር እና ወከባ እያስተናገዱ መሆኑ ተሰማ

– አውሎ ሚዲያ 13 ባልደረቦቹ ታስረዋል

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 25፣ 2013 ― ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ በርካታ የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች እስር እና ወከባ እያስተናገዱ እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡

እስር ካስተናገዱት መካከል በበይነ መረብ መረጃዎች እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን የሚያቀርበው አውሎ የተሰኘው ሚዲያ የሚገኝበት ሲሆን፣ 13 የሚዲያው ጋዜጠኞች እና ሌሎች ሠራተኞች በፀጥታ አካላት ከሥራ ቦታቸው ተወስደው በፌዴራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት መራሰራቸውን አምባ ዲጂታል ከምንጮቹ ሰምቷል።

በተመሳሳይ ሌላኛው የበይነ መረብ ሚዲያ ኢትዮ ፎረም ባልደረባ የሆነውና ከሳምንት በፊት ድብደባ የተፈፀመበት አበበ ባዩ፣ ትላንት ምሽቱን 3፡20 አካባቢ በድጋሚ የፌደራል ፖሊስን የደንብ ልብስ በለበሱና ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ መወሰዱን ሚዲያው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ገልጧል፡፡

ጋዜጠኛው የት እንደተወሰደ እንዳልታወቀ የገለጸው ኢትዮ ፎረም፣ ‹‹አብረውት የነበሩት ጓደኞቹም የጋዜጠኛ አበበን መታሰር ለየትኛውም አካል ከተናገሩ እንደሚገደሉ ተነግሯቸዋል›› ብሏል፡፡

ከነዚህ ሁለት የበይነ መረብ ሚዲያዎች በተጨማሪ ሌሎች በርከት ያሉ ጋዜጠኞች ለእስር እየተፈለጉ እንደሚገኙና፣ የፀጥታ አካላትም ወከባ እየፈጸሙባቸው እንደሚገኝም አምባ ዲጂታል ሰምቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ትላንት ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ መወሰዱ የተነገረው የኢትዮ ፎረም ባልደረባ የሆነው አበበ ባዩ ላይ ከአስር ቀናት በፊት ሰኔ 14፣ 2013 በመኪና ታፍኖ ወደ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ተወስዶ ድብደባ፣ እንግልት እና ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ከጋዜጠኛው መስማቱን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡

የጋዜጠኛውን ጥቃት አስመልክቶ ሲፒጄ አናገርኳቸው ያላቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጄይላን ዐብዲ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ስለ ጉዳዩ የሰማነው ነገር የለም እንዳሉት ገልጧል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የሲፒጄ አፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጌላ ኩዊንታል ጋዜጠኛ አበበ ባዩ ላይ አፈና እና ጥቃት ያደረሱ ሰዎች ከተጠያቂነት ሊያመልጡ እንደማይገባና የመንግሥት ባለሥልጣናትም ጥቃት አድራሾቹ ላይ ምርመራ በማድረግ ለድርጊታቸው ተጠያቂ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አክለውም በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች በነጻነት ሥራቸውን ሊከውኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ ጋዜጠኞቻቸው እስር እና ጥቃት ያስተናገዱት የበይነ መረብ ሚዲያዎች በአሁኑ ወቅት ሥርጭታቸውን ማቋረጣቸውን መመልከት ችለናል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ስትጠቀስ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ መሻሻሎች ቢታዩም፣ ኢትዮጵያ በጋዜጠኞች እስር መልሶ ደረጃዋ ማሽቆልቆሉን የመብት ተሟጋች ተቋማት በማንሳት ላይ ይገኛሉ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img