Saturday, October 12, 2024
spot_img

ፓርላማው ከጣሊያንና ከፈረንሣይ መንግሥታት ጋር የተደረጉ የመከላከያ ስምምነቶችን አፀደቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 23፣ 2013 ― የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፈረንጆቹ በመጋቢት 2019 እና በሚያዝያ 2019 የኢትዮጵያ መንግሥት ከጣሊያንና ከፈረንሣይ መንግሥታት ጋር በመከላከያ ዘርፍ ያካሄዳቸውን ስምምነቶች በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡

ከሁለቱ የአውሮፓ አገሮች ጋር የተደረገው ስምምነት በዘርፉ በትምህርት፣ በሥልጠናና በደኅንነት ድጋፎች ላይ አብሮ ለመሥራት የታለመ መሆኑን፣ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ በመከላከያ ዘርፍ ትብብር ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያን ሠራዊት አባላት ወታደራዊ የቴክኒክ አቅምና ክህሎት ለማጎልበት፣ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አክለው አስረድተዋል፡፡

ከፈረንሣይ መንግሥት ጋር የተደረገው ስምምነት የላኪው አገር አውሮፕላኖች በተቀባዩ አገር የአየር ክልል ውስጥ መብረርና ማረፍ እንዲችሉ፣ እንዲሁም መርከቦች መልህቃቸውን እንዲጥሉ ወይም እንዲያቆሙ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ትላንት ሰኔ 22 በዋለውና 288 የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት ስድስተኛ ዓመት 16ኛ መደበኛ ስብሰባ በሙሉ ድምፅ የፀደቀው የሁለቱ አገሮች ስምምነት፣ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅምና ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም አስታውቀዋል፡፡

ለሁለት ዓመታት ያህል በውይይት ላይ እንደነበረ የተነገረለት የስምምነት ሰነድ፣ የካበተ ልምድ ካላቸው አገሮች ጋር መሥራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡

ከፈረንሣይ መንግሥት ጋር የተደረገው ስምምነት የጋራ በሆኑ የመከላከያና የፀጥታ፣ እንዲሁም ወታደራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ሰላም ለማስከበር የሚረዳ ሥልጠና የፈረንሣይኛ ቋንቋን ጨምሮ በወታደራዊ ትምህርት ሥልጠና፣ በወታደራዊ ቴክኒክ አቅም ግንባታና በመሳሰሉት በተዋዋይ ወገኖች አስፈላጊ ናቸው ተብለው የተለዩ ጉዳዮችንም ያመለክታል ተብሏል፡፡

ከፈረንሣይ ጋር የተደረገው ስምምነት አንቀጽ ስምንት የላኪው አገር ወታደራዊ አባላት በተቀባዩ አገር ውስጥ በሚወሰነው መሠረት ወታደራዊ የደንብ ልብስ እንዲጠቀሙ እንደሚደነግግ የሪፖርትር ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img