Saturday, October 12, 2024
spot_img

የፌዴራል መንግሥት ከዚህ በኋላ በትግራይ ለሚከሰት ችግር ተጠያቂ እንደማይሆን አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 23፣ 2013 ― የፌዴራሉ መንግሥት ከዚህ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለሚከሰት ችግር ተጠያቂ እንደማይሆን አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመቐለ ለቆ በመውጣቱ፣ የፌዴራል መንግስት ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል ዙሪያ ለሚኖር ችግር ተጠያቂ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትም ‹‹ከዚህ በኋላ ርዳታ ደረሰ አልደረሰ ብለው የፌዴራ መንግስትን ሊጠይቁ›› እንደማይገባ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ሙሉ ኃላፊነቱን አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሕወሃት እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት፤ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ኪሳራ እንደዳረጋት ገልጸው በልማት ሂደቱ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል፡፡

ሕወሃት የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንደጣለ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው ሱዳን፤ የኢትዮጵያን ሉኣላዊ ድንበር ጥሳ እንድትገባ አጋልጦ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ክልል በተደረገ ዘመቻ፤ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ መውጣቱም ተገልጿል፡፡

መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ከመቀሌ ያስወጣው በመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡ መንግስት የተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ከመቀሌ ያስወጣው፤ ሀገርን ለተጨማሪ የሐብት ብክነት ላለመዳረግ መሆንም ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጦር በማንኛውም ጊዜ ወደ ትግራይ የመመለስ ሙሉ አቅም እንዳለውም ሚኒስትር ደኤታው ማብራራታቸውን የዘገበው አል ዓይን ሚዲያ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img