አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 23፣ 2013 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትላንት ማምሻውን በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፖርክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በተገኙበትና በምርጫው ወቅት መገናኛ ብዙኃን በነበራቸው አስተዋጽኦ ዙርያ ምሥጋና ባቀረቡበት ወቅት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት መቐለ ከተማን የለቀቀው የታክቲክ ለውጥ በማድረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ እስካሁን ድረስ በትግራይ ክልል ለእርዳታ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን በተናገሩበት መድረክ፣ በተረጂዎች አማካኝነት ርዳታው ‹‹ጁንታ›› ሲሉ ለሚጠሩት የሕወሃት ቡድን ሲደርስ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይህ ይደረግ የነበረው ሁለት ልጅ ያለው 5 እና 7 ልጆች አሉኝ እያለ በተረጂዎቹ አማካኝነት እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩ በሕዝብ ነው እየተገደለ ነው ያለው፣ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ጦሩ እንዲቆይ ካደረግን ጦሩ ወዳልተፈለገ ርምጃ ሊገባ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
ይህ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ ከውስጥም ከውጭም ያሉ አካላት ማናቸውም እየተደረገ ላለው ድጋፍ እውቅና መስጠት የፈለገ የለም ያሉት ዐቢይ፣ መንግሥት ይህን ሁሉ ተቋቁሞ እየሰራ የነበረ ቢሆንም፣ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከውስጥ የሚደርሱበት ጫናዎች እና በመንግስት ላይ ከውጭ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች የሚከፈለው ዋጋ ለማን ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
‹‹ምንም አቅም የሌለው›› ያሉትን የሕወሃት ቡድን አዲሱ ታክቲክ በተራዘመ ጦርነት ሀገሪቱም አብራ እንድትዳከም እና እንድትወድቅ ማድረግ ነው ያሉም ሲሆን፣ እኛም ይህን በመረዳት ‹‹እየሞተ ካለ ቡድን ጋር አብሮ ላለመሞት›› የታክቲክ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገን ነበር ብለዋል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሳምንት መወያየታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ውሳኔው መከላከያ ‹‹ደጀን ወደሚያገኝበት አካባቢ እንዲመጣ›› ሕዝቡም ከስህትቱ የሚማርበት የጥሞና ጊዜ ለመስጠት እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብም እውነታውን የሚረዳበት ሁኔታን መፍጠር አለብን በሚል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአገር መከላከያ ጦር ትግራይን ለቅቆ እንዲወጣ ከወሰኑ በኋላ ምሽቱን እስከ እኩለ ሌሊት ከብዙ የዓለም መሪዎች የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ በተለይ ጦሩን ‹‹ሲከስሱ እና ሲወቅሱ›› ነበሩ ያሏቸው አገራት በጦሩ መውጣት መበሳጨታቸውን ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን እንዲቀርጹት ተከልክለዋል በተባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ደርሶበታል ያሉትን በደል አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል መከላከያ ለቆት የወጣው የመቀለ ከተማን በተመለከተ፣ አሁን መቀሌ ምንም አይነት የስበት ማዕከል አይደለችም፤ ምንም ለወታደራዊ ስትራቴጂነት የቀራት ነገር የለም ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል እና በሌሎች ክልሎች መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ግን እኩል ሆኗል ወይም ከዛ በታች ወርዷል ማለታቸው ነው የተሰማው፡፡
በተጨማሪም እኛ ትግራይን ተቆጣጥሮ እንደ ቅኝ ገዢ የመቆየት አላማ አልነበረንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚስተካከለውን አስተካክሎ ወደ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች መመለስ ነበር አጀንዳችን ብለዋል፡፡
አሁን የሚመሩት መንግሥት ፊቱን ወደ ሕዳሴ ግድብ እንደሚያዞርና የአገር መከላከያ ሠራዊትም ትኩረት ወደዚያው መሆኑን መጠቆማቸውን በዝግጅቱ የታደሙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ካሰፈሩት ማስታወሻ ተመልክተናል፡፡