አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 ― ሱዳን የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ በኢትዮጵያ የቀረበውን ሐሳብ መቃወሟን ሬውተርስ ሥማቸው እንዳይገለጽ ፈልገዋል ያላቸውን አንድ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ከፍተኛ ባለሥልጣኑ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ያቀረበችው ሐሳብ ‹‹ተጨባጭ ያለሆነ›› እና ‹‹ጊዜ ለመግዛት የቀረበ›› ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ጨምረውም እንዲህ አይነቱ ሐሳብ መቅረብ ያለበት ሁሉንም ወገኖች ባካተተ ሁኔታ በአፍሪካ ሕብረት የድርድር ጥላ ስር መሆን እንደነበረበት ተናግረዋል።
በስም ያልተጠቀሱት ባለሥልጣኑ ኢትዮጵያ የውሃ ድርሻን በተመለከተ ‹‹ሊሆን የማይችሉ ቅደመ ሁኔታዎችን›› ያቀረበች ሲሆን፣ ሱዳን ይህን ሐሳብ ከድርድር ማዕቀፍ ውጪ ነው ብላ እንደምታስብ ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት የዜና ወኪሉ ለኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ጥያቄ አቅረቤ የነበረ ቢሆንም ምላሽ አላገኘሁም ብሏል፡፡
ባለፈው ሳምንት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ማሐዲ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በተከሰተው አለመግባባት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባና ኢትዮጵያ ‹‹በተናጠል›› ግድቡን በውሃ ከመሙላት እንድትታቀብ እንዲያደረግ በደብዳቤ መጠየቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ዓመት ያከናወነውን የመጀመሪያውን ውሃ ሙሌት ተከትሎ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ለማካሄድ ያቀደችው ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ሊያስቆም የሚችል ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ሲገልጽ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡
ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በዚህ ዓመት የክረምት ወራት ውስጥ ካልተከናወነ ከባድ ኪሳራን ሊያስከትል እንደሚችል የገለጸው መንግሥት፣ በግድቡ ላይ ተቃውሞ ከሚያደርጉት አገራት ጋር ድርድሩ እየተካሄደ ውሃ የመሙላት ሥራው እንደሚቀጥል ገልጧል፡፡