አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሳምንት በፊት የተካሄደው አገራዊ ምርጫ ወቅት በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ ከጠቀሳቸው ከነዚህ ሪፖርቶች ውጪ፣ የአገራዊ ምርጫው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊና በብዙ መልኩ የተሳካ እንደነበር ነው የገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ 94 ባለሙያዎችን የያዙ 35 የክትትል ቡድኖች በማሰማራት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ምርጫው በተካሄደባቸው 7 ክልሎች በሚገኙ 99 ምርጫ ክልሎች እና 404 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
በክትትሉ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው እለት ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተቶችን መመልከቱን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ሆኖም በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳልታየ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል፡፡
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ‹‹በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለ የጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ በመሆኑ፤ የምርጫው ዕለት ሂደት ሰላማዊ፣ ሥርዓትን የተከተለና በአብዛኛው ሁኔታ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩበትና በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ነበር›› ብሏል።
ነገር ግን ‹‹አዎንታዊና አበረታች ናቸው›› ያላቸው እነዚህ ርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው የጠቆመው፡፡
‹‹ጥቃቱን የፈጸሙ፣ ግድያና የአካል ጉዳት፣ እስርና እንግልት ያደረሱ ሰዎች ላይ ሁሉ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ››ም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ምርጫ ቦርድ ለክትትል ባለሙያዎቹ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለመግባት የሚያስችላቸውን ካርድ (ባጅ) ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት በየምርጫ ጣቢያዎቹ ያለውን ሁኔታ በወጉ ለመከታተል ተቸግሮ እንደነበርም ነው ያስታወቀው፡፡
የምርጫውን መካሄድና በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በምርጫው መሳተፋቸውን ያወደሱት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንዔል በቀለ፣ ክትትል ባደረግንባቸው ቦታዎች የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ባንመለከትም ጥሰቶች እንደነበሩ ግን ሐቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡