Sunday, September 22, 2024
spot_img

ከ2 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በዛሬው እለት ከሳዑዲ ዐረቢያ ይመለሳሉ ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 19፣ 2013 ― ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሳዑዲ ዐረቢያን ድንበር ጥሰው ሲገቡ በሳዑዲ ፖሊስ የተያዙ እና የሳዑዲ የመኖርያና የሥራ ፈቃድ ሕግጋትን ተላልፈው በመገኘታቸው በስደተኞች ማቆያ ጣብያዎች ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ከቆዩ ኢትዮጵያውያን መካከል 2 ሺሕ የሚሆኑት በዛሬው እለት እንደሚመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

እነዚህ እስረኞች በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ረዘም ላለ ግዜ በእስር በመቆየታቸው ሳቢያ በቤተሰቦቻቸውና በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቡና ጫና አሳድሮ ከመቆየቱ ባሻገር የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገርያ ሆኖ መቆየቱን ያስታወሰው ጽሕፈት ቤቱ፣ በቅርቡ መንግስት እነዚህ እስረኞች በሙሉ ወደ አገር እንዲመለሱ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጧል፡፡

ይህን ለማሳካት የሁለቱ አገራት መንግስታት ባደረጉት ስምምነት መሰረት፣ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ ዜጎቹን በስፋት ወደ አገር ቤት የመመለስ ሂደት ለማሳካት ከኢትዮጵያ ወገን ቀዳሚ ልዑክ ቡድን ተልኮ ከሳዑዲ አረቢያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ጥልቅ ውይይት በማድረግ ዜጎችን የማስመለስ ስራ መመቻቸቱንም አሳውቋል፡፡

ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤቱ፣ በዚሁ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በየቀኑ እስከ ስድስት በሚደርሱ የሳዑዲ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች በማቆያ ጣብያዎች የነበሩ ዜጎች ይመለሳሉ ያለ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ቁጠራቸው ከ2 ሺሕ በላይ የሆኑ ዜጎች በመጀመሪያ ዙር እንደሚመጡ ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በራሳቸው ወጪ ወደ አገር ቤት ለመግባት ለሚሹ ኢትዮጵያውንም በቅርቡ ሁኔታዎች በስፋት ይመቻቻሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውች ጉዳይ አሳውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img