አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 18፣ 2013 ― የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባልደረባው ኢንጂነር እምብዛ ታደሰ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ መገኘቱን አስታውቋል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ በግምት ከቀኑ ሰባት ሰዓት በኃላ ወጣቱ እንጂነር እምብዛ ታደሰ ከቢሮ ወደ መቀሌ አሉላ አባ ነጋ የአየር ማረፊያ ለመጓዝ በተዘጋጀበት፣ ማንነታቸው ባልታወቁ አፋኞች በኃይል ተወስዶ ደብዛው መጥፋቱን አስታውሷል፡፡
ኋላም በፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ኃይሎች በተከናወነ አሰሳ፣ ኢንጂነር እምብዛ ‹‹በጨካኝ የከተማ ሽብር ተልእኮ አስፈፃሚ ወንጀለኞች‹‹ በዓይደር ልዩ ስሙ ማረሚያ ቤት በተባለ ስፍራ ተገድሎ ለጅቦች በተጣለበት ትላንት ከረፋዱ አምስት ሰዓት ቁርጥራጭ የሰውነት አካላቱን በመለየት በተጨማሪ ምርመራ በጭካኔ መገደሉን ማረጋገጥ መቻሉን ነው የገለጸው፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኢንጂነር እምብዛ ታደሰና ባለፋት ተከታታይ ወራት በክልሉ በንፁሐን አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶችን በጥብቅ እንደሚያወግዝ ገልጿል።
አስተዳደሩ ይህ ‹‹በእጅጉ ከሰብአዊ ፍጡት የማይጠበቅ ነው›› ያለው ግድያ እየተፈጸመ ያለው፣ ‹‹ትግራይ ላጋጠማት ቸግር መፍትሔ አካል ለመሆን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የተልእኮ አቅጣጫ በመውሰድ ወገኖቻች ለተጨማሪ ሞትና ስቃይ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በዘመቻ መልክ በቅንጅት ለመተግበር ሊፈጠር የሚችለውን ተጨማሪ ቀውስ እንዳይባባስ ትንቅንቅ በተያዘበት ወቅት እንደሆነ በመግለጽ፣ ይህ የትግራይን እንባ በማበስ መስዋእት የሚያስከፍል የሰማእት ወጣቶች ተልእኮ ለአረመኔዎች ደንታ የማይሰጥበት የጭካኔ ጠርዝ መኖሩን እያስቃኘን ይገኛል›› ብሏል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጨምሮም ‹‹የትግራይ የቁርጥ ቀን የነፍስ አድን ሙያተኞች ሕይወት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ›› መገደል ብናረዳም፣ የምላሹ መላም እጅግ የፈጠነ፣ የተሰላና አስተማሪ መሆኑን ለአጥፊዎቹ ከወዲሁ በማስገንዘብ ነው በማለት አስጠንቅቋል፡፡
በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳድር የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ ማግልገሉ የተነገረው ኢንጂነር እምብዛ ታደሰ፣ ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበር።