Sunday, November 24, 2024
spot_img

ባልደራስ ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራትን ታዝቤያለሁ አለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 18፣ 2013 ― ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) የስድስተኛውን ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ድምጽ አሰጣጥ ተከትሎ ‹‹ኢትዮጵያ መቼ ይሆን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚኖራት›› በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫው፣ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራትን ታዝቤያለሁ ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በምርጫው የተከሰቱ ችግሮችን በጥልቀት እየመረመርኩ እገኛለሁ ያለው ፓርቲው፣ በእስካሁን በደረሰበት ሁኔታ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ናቸው ያላቸውን ተግባራት ዘርዝሯል፡፡

ከነዚህ መካከል ድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት የተሰየሙ የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ የገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ የሚረዳ ገለጻ ሲያካሂዱ የፓርቲዎች ወኪሎች እርምት እንዲያደርጉ ቢያስገነዝቡም፣ አስፈፃሚዎች ብልሹ አሠራራቸውን አለማስተካከላቸው በችግርነት የታየ ጉዳይ መሆኑን አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያልነበሩ አዳዲስ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ ‹‹ማንነታቸው የማይታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ሲሰጡባቸው መቆየታቸው፣ አቅመ ደካሞችን፣ በእድሜ የገፉትን እና የአካል ጉዳተኞችን የመንግሥት ካድሬዎች ከምርጫ ህጉ ውጭ በማገዝ ስም በሚስጥር ድምፅ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ይዘዋቸው በመግባት ጫና እየፈጠሩ የሚፈልጉትን ማስመረጣቸው፣ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የባልደራስን የምርጫ ውጤት ቁጥሮች እየቀነሱ እንዲጻፉ መደረጋቸው›› እንዲሁም ‹‹ባልደራስ የተመረጠባቸውን ወረቀቶች በስልት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ወይም የባከኑ ውጤቶች››> መኖራቸውን አስቀምጧል፡፡

በተጨማሪም የገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለችግረኛ ሰዎች ‹‹የተለያዩ መደለያዎች በመስጠት የሕዝብን ገንዘብ ለሥልጣን መሸመቻ ማድረጉን›› በማንሳት፣ ተግባሩ ‹‹በምድር ቀርቶ በፈጣሪ ዘንድ ይቅር የማያሰኝ›› ነው ብሎታል፡፡

‹‹ቀን በፀሐይና በዝናብ፣ በምሽት እና በሌሊት ደግሞ በብርድ እንዲንገላታ የተደረገበትን ደባ ተቋቁሞ የተሰለፈው አዲስ አበቤ፣ ድምፁን ለማን እንደሰጠ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንቅቆ ያውቃል›› ያለው ፓርቲው፣ መራጮቹን በማመስገን ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 የተካሄደውን የምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img