Thursday, November 21, 2024
spot_img

ኢዜማ እና ነእፓን ጨምሮ ስምንት ፓርቲዎች በወላይታ ዞን የተካሄደው ምርጫ ውድቅ እንዲደረግ ጠየቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 17፣ 2013 ― በደቡብ ክልል ወላይታ የተወዳደሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ነጻነት እና እኩልነት (ነእፓ)ን ጨምሮ ስምንት ፓርቲዎች፣ በዞኑ ባሉት ሰባት የምርጫ ክልሎች የተደረገው ምርጫ በገዢው ፓርቲ ስለተጭበረበረ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ውድቅ እንዲያደርገው ለምርጫ ቦርድ በጋራ በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡

ደብዳቤውን ለምርጫ ቦርድ የጻፉት ኢዜማ፣ ነእፓ፣ ዎብን፣ ዎህዴግ፣ እናት፣ ኅብር ኢትዮጵያ፣ ኢሶዴፓ እና ኢህአፓ ፓርቲዎች፣ በዞኑ ተፈጽሟል ያሉትን የምርጫ ማጭበርበር ዘርዝረዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በወላይታ ሰባት የምርጫ ክለሎች ተፈጽመዋል ካሏቸው ተግባራት መካከል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢዎች በሌሊት ተገኝተው ቃለ ጉባኤ ላይ እንዳይፈርሙ መከልከል፣ ድብደባ እና አፈና፣ የአስፈጻሚዎችን ፊርማ አስመስሎ መፈረም፣ እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 የሆኑ ታዳጊዎችን ሐሰተኛ መታወቂያ በመስጠት ለመራጭነት ማሳተፍ፣ ከድምጽ አሰጣጥ ሒደት በፊት በሳጥኖች የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን መክተት፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች መራጩን ማዋከብና ለመራጮች ምልክት እያደረጉ መስጠት እንዲሁም የቀበሌ ታጣቂዎች በድምጽ መስጫ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው አምፑልን መምረጣቸውን ዘርዝረዋል፡፡

እነዚህ ስምንቱ ፓርቲዎች፣ በርካታ ችግሮች ታይቶበታል ያሉትን ምርጫ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረቡ አቤቱታዎቸን ተመልክቶ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ምርጫውን እንዲሰርዘው ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ምርጫ ቦርድ በነዚህ የምርጫ ክልሎች ‹‹የተጨበረበረ ነው›› ያሉትን ምርጫ፣ ቅሬታዎች ተመልክቶ ማስተካከያ የማያደርግ ከሆነ፣ በዞኑ ምርጫ ባልተካሄደባቸው ቀሪ ስድስት የምርጫ ክልሎች ‹‹የመወዳደር ሞራላችንን ክፉኛ የተጎዳብን በመሆኑ››፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ‹‹ራሳችንን እናገላለን›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስምንቱ ፓርቲዎች ቅሬታ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img