Saturday, October 12, 2024
spot_img

የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ በገበያ ሥፍራ የቦንብ ጥቃት ተጎጂዎች ሕክምና ተከልክለዋል በሚል ድርጊቱን አወገዘ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 17፣ 2013 ― የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ማክሰኞ ሰኔ 15 በትግራይ ክልል ከመቐለ በስተምዕራብ 20 ኪሎ ሜትር ላይ ቶጎጓ በሚባል ሥፍራ ተፈጽሟል በተባለ የአውሮፕላን ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሐን ጉዳት እንደደረሰባቸው በመጥቀስ ጥቃቱን አውግዟል፡፡

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው፣ እነዚሁ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና እንዳያገኙ በጸጥታ ኃይሎች ክልከላ ተፈጽሟል በሚልም ድርጊቱን ኮንኗል፡፡

የአገሪቱ መንግሥት ተቀባይነት የሌለው ነው ያለውን ይህን ድርጊት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰዎች የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱበት ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የደረሰው ጥቃት በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲደረጉም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት በመግለጫው ማሳረጊያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተፋላሚ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና ለዜጎች የሰብአዊ አቅርቦት እንዲደርስ ጠይቋል፡፡

በትግራይ ክልል ቶጎጓ በተባለ አካባቢ በገበያ ሥፍራ ተፈጽሟል በተባለው የአውሮፕላን የቦንብ ጥቃት፣ የሁለት ዓመት እድሜ ያለው ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሲሞቱ፣ የአካል ጉዳት የደረሳባቸው ሰዎች መኖራቸውንም የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

ጥቃቱ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች በአገር መከላከያ ሠራዊትና በሕወሃት ኃይል መካከል ያገረሸውን ከባድ ውጊያ ተከትሎ የተከሰተ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ጥቃቱን አስመልክቶ የሕወሃት አመራሩ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ መከላከያን ተጠያቂ ያደረጉ ቢሆንም፣ ቢቢሲ የአገር መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮለኔል ጌትነት አዳነ ንጹሐንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንዳልተፈጸመ ነግረውኛል ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img