Sunday, October 6, 2024
spot_img

የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ አዲስ አልበም ለገበያ ሊቀርብ ነው

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 16፣ 2013 ― ባለፈው ዓመት ሰኔ 22፣ 2012 በአዲስ አበባ ከተማ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ያለፈው በኦሮሚኛ ቋንቋ የዘፈን ሥራዎቹ የሚታወቀው ሐጫሉ ሁንዴሳ አዲስ አልበም ለገበያ ሊቀርብ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ለድምጻዊው ሦስተኛ የሆነው ይህ አልበም ቀድሞ ያዘጋጃቸው ሥራዎችን የያዘ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡ የአልበሙ ርእስ ‹‹ማል ማሊሳ›› እንደሚሰኝ አልበሙን ለማስተዋወቅ ከተከፈተው የፌስቡክ ገጽ ላይ ተመልክተናል፡፡

ፖለቲካዊ መልዕክት ባላቸው ተወዳጅ የኦሮሞ የትግል ሙዚቃዎች አቀንቃኝነት የሚታወሰው ሐጫሉ ሁንዴሳ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የለቀቀው በመላው አገሪቱ ተወዳጅ የሆነለትን ‹‹ሳኚ ሞቲ›› የተሰኘውን አልበሙን ነበር፡፡

አሁን ሦስተኛ አልበሙ ለገበያ የሚቀርብለት አቀንቃኙ፣ ሁለተኛ አልበሙን የለቀቀው ወደ አሜሪካ ባቀናት ወቅት የነበረ ሲሆን፣ ‹‹ዋኤ ኬኛ›› (የእኛ ነገር እንደማለት) የሚል ርእስ አለው፡፡

ከመሞቱ ቀድሞ በነበሩ ዓመታት ለትግል በዋለው ‹‹ማለን ጂራ›› እና ኋላም የአገሪቱ ፖለቲካዊ አሰላለፉ ሲቀየር የለቀቀው ‹‹ጂራ›› የተሰኙት ሥራዎቹ የአድማጮችን ቀልብ በሥፋት የያዙ ነበሩ፡፡

በ36 ዓመቱ የተቀጨው ሐጫሉ ሁንዴሳ፣ አሟሟቱ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ልብ የሰበረ እንዲሁም ሞቱ ባስከተለው ቁጣ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ለከፍተኛ ሁከት ተዳርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img