Monday, November 25, 2024
spot_img

ሱዳን የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ስብሰባ እንዲጠራ ጠየቀች

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 16፣ 2013 ― የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በተከሰተው አለመግባባት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃለች፡፡

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጽሑፍ ባቀረበው ጥያቄ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ ግድቡ ‹‹በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ደኅንነት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ›› እንዲወያይ ጠይቋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማሪያም አልማሕዲ አማካይነት ለጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊ በተጻፈው ደብዳቤ፤ ሱዳን ኢትዮጵያ ‹‹በተናጠል›› ግድቡን በውሃ ከመሙላት እንድትታቀብ የምክር ቤተ አባላት ጥያቄ እንደቀረበላቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በህዳሴ ገድበ ጉዳይ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ምንም ውጤት ሳያስገኝ በመቅረቱ በግድቡ የውሃ አሞላል ዙሪያ ያለው ውዝግብ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ በራሷ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብ ከ60 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ለልማት እጅግ አስፈላጊ ፕሮጀክት መሆኑን በመግለጽ ግንባታውን ቀጥላለች።

በተቃራኒው ሱዳንና ግብጽ ደግሞ በግድቡ የውሃ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ ላይ አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት ካልተደረሰ ከዐባይ ወንዝ በምናገኘው ውሃ ላይ ተጽእኖ ስለሚፈጠር ግድቡ ሕዝባችንን ለችግር ያጋልጠዋል በማለት ሲቃወሙ ቆይተዋል።

የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በቀጣይ ሐምሌ ወር እንደሚሞላ መንግሥት ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img