Tuesday, December 3, 2024
spot_img

በአምስት ተጨማሪ የምርጫ ክልሎች በነገው ዕለት ምርጫ እንደማይካሄድ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሰኔ 13፣ 2013 ― በነገው ዕለት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አምስት የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በምርጫ ክልሎቹ ድምጽ እንዳይሰጥ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ተነካክቶ መገኘት እና የምርጫ አስፈጻሚዎች እጥረት እንደሚገኝበት ቦርዱ ገልጿል።

ምርጫ ከማይካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሶስቱ የሚገኙት በአማራ ክልል ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል መሆኑን የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ምርጫ የማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ደምቢያ፣ ተውልደሬ 1 እና ተውልደሬ 2 ሲሆኑ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ግንደ በረት እና ነጌሌ የምርጫ ክልሎች ናቸው።

በደምቢያ፣ ተውልደሬ 1 እና ተውልደሬ 2 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁሶች እና ሰነዶች የሚታሸጉባቸው ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው መገኘታቸውን የገለጹት ሶልያና፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችም ተነካክተው ተገኝተዋል ብለዋል።

ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ በደምቢያ የምርጫ ክልል የሚገኙ ሶስት የምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት ቦርዱ ለፌደራል ፖሊስ ጥያቄ ማቅረቡንም አስረድተዋል።

በተውልደሬ 1 እና ተውልደሬ 2 የምርጫ ክልሎች ላይ የተፈጠረውን ችግር ፖሊስ በምርመራ እንዲያጣራ ቦርዱ መጠየቁንም አክለዋል። በአማራ ክልል በመተማ የምርጫ ክልል እና በደቡብ ክልል ስቄ 1 እና ስቄ 2 የምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የምርጫ ቁሳቁሶች እና ሰነድ ማሸጊያ የሆነው ሰማያዊ ሳጥን በምርጫ አስፈጻሚዎች ቢከፈትም፤የጽምጽ መስጫ ወረቀቶች ባለመነካካታቸው በእነዚህ ቦታዎች ምርጫው እንደሚካሄድ ሶልያና አብራራተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በሚገኘው ኔጌሌ የምርጫ ክልል፤ ነገ ድምጽ የማይሰጥበት ምክንያት በምርጫ ክልሉ ከተመዘገቡ አንድ የግል ዕጩ ጋር በተያያዘ እንደሆነ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል።

የግል ዕጩው በምርጫ ክልሉ ለመወዳደር ከምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፊኬት ቢሰጣቸውም “በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ አልተካተትኩም” ብለው ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት ቦርዱ ጉዳዩን ለማጣራት በሚል በቦታው ምርጫ እንዳይካሄድ መወሰኑን ሶልያና መናገራቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img