አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 12፣ 2013 ― በደቡብ ክልል በአማሮ ወረዳ ባለፉት ሁለት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች የሚሰነዝሩትን ጥቃት ዘመቻ አጠናክረው መቀጠላቸውን የወረዳው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ በማኀበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
እንደ ቢሮው ታጣቂዎቹ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሰኔ 10፣ 2013 በጎልቤ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ፈጽመው የአንድ ሰው ሕይወት ሲቀጠፍ፣ ሁለት አርሶ አደሮች ቆስለዋል፡፡
የኮሚኒኬሽን ቢሮው በምእራብ ጉጂ ዞን በጋላና እና ሱሮ ባርጉዳ ወረዳዎች በሕገ ወጥ መንገድ ይንቀሳቀሳሉ ያላቸው እነዚሁ ታጣቂዎች፣ በትላንትናው ዕለት ዐርብ ሰኔ 11 በአማሮ ወረዳ ዳኖ ቀበሌ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ሕዝቡ የጸጥታ አካላት እንዲታደጉት ጥሪ በማሰማቱ የጸጥታ አስከባሪዎች ወደ ቀበሌው ገብተው ተከላክሏል፡፡
በዚሁ ወቅት አንድ የልዩ ኃይል አመራር ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጉንም ገልጧል፡፡
የወረዳው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ጥቃት አድራሾቹ የታጠቁ ኃይሎች፣ አሁንም በተለያዩ ቡድን ሆነው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ነው ያመለከተው፡፡
የደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በተደጋጋሚ በሚያደርሱት ጥቃት ሥሙ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው፡፡