Friday, November 22, 2024
spot_img

ዐቃቤ ሕግ ጄኔራል ሰአረ መኮንንን በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በሞት እንዲቀጣ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 11፣ 2013 ― የቀድሞ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኮንን ላይ ግድያ በመፈጸም ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው አስራ አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብር እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ግንቦት 27፣ 2013 በዋለው ችሎት አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ጄኔራል ሰአረ መኮንን እና ጓደኛቸው ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራን የመግደል ወንጀል መፈጸሙን የቀረበበት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ያስረዳል ሲል የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም ችሎቱ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ለመመልከት ለዛሬ በተሰጠ ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት በችሎቱ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ በሞት እንዲቀጣለት ጠይቋል፡፡

የአስራ ዐለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ጠበቆች በበኩላቸው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው የሞት ቅጣት ማክበጃው ከወንጀል ሕግ 117 ንዑስ ቁጥር 1 ድንጋጌ ውጪ ነው በማለት መቃወሚያ አሰምተዋል፡፡

ተከሳሹ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የሁለት ልጆች አባት መሆኑ እንዲሁም እናትና አባቱን የሚያስተዳድር መሆኑን በማቅለያ ተጠቅሶ፣ ይህን የሚያረጋግጥ ከጎንደር ዞን ከጎንደር ዙሪያ ምክር ቤት ከሰንዳባ ቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ማስረጃ በጠበቆቹ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሹ ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለበት ጊዜ በፊት በልጅነቱ ውትድርና ተቀጥሮ ሀገሩን እና ህዝብን ሲያገለግል እንደነበር በዓቃቤ ህግ ምስክሮች ጭምር የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ አስተዋጽኦ ዝም ብሎ የሚጣል አደለም ሲሉ ጠበቆቹ በማቅለያነት እንዲመዘገብ ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ጠበቆቹ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ማቅረብ የሚገባቸው በጽሑፍ ነበር፣ ሆኖም ያቀረቡት ማስረጃ ትክክለኛነትን ማረጋገጥ ስላለብን ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከቅጣት በፊት ዓቃቤ ሕግ የማስረጃ አግባብነትን አጣርቶ እንዲቀርብ በማዘዝ መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 21፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img