Wednesday, October 9, 2024
spot_img

በሰዎች የመነገድ ወንጀል የፈጸመው ኪዳኔ ዘካሪያስ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 11፣ 2013 ― በሰዎች የመነገድ ወንጀል በመፈጸም ተከሶ ጉዳዩን እየተከታተለ ባለበት ከወህኒ ቤት ያመለጠው ኪዳኔ ዘካሪያስ በሌለበት በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት የዐቃቤ ሕግ መረጃ አመልክቷል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ባሰፈረው ዝርዝር ክስ የእድሜ ልክ እስር የተወሰነበት ኪዳኔ ዘካሪስ፣ ወደ ስደት ለማቅናት ከኢትዮጵያ ተነስተው በሱዳን በኩል አቋርጠው ሊቢያ ‹ቢን ወለድ› በሚባል ቦታ ደርሰው የነበሩትን ሟች ዳንኤል ጥላሁን እና ሟች መሐመድ ዓለሙን በጦር መሳሪያ ታግዞ በማገት፣ ‹‹እኔ ገዝቻችኋለሁ እያንዳንዳችሁ 5 ሺሕ 500 ዶላር ካልከፈላችሁ እዚሁ ትሞታላችሁ›› በማለት እጅና እግራቸውን በገመድ በማሰር በኤሌክትሪክ ገመድ በመግረፍና በማስገረፍ፣ ላስቲክ በእሳት አቅልጦ በሰውነታቸው ላይ በማንጠባጠብ፤ በመያዣነት በመያዝ ከሟች መሐመድ ዓለሙ ቤተሰቦች በፌቨን ከበደ ስም 155 ሺሕ ብር ገቢ ያስደረገ ሲሆን፣ በአባሪው በ2ኛ ተከሳሽ አካውንት ላይ ደግሞ ብር 30 ሺሕ ገቢ እንዲደረግለት አድርጓል፡፡

በተመሳሳይ ከሟች ዳንኤል ጥላሁን ቤተሰቦችም 187 ሺሕ ብር በአካውንቱ ገቢ አስደርጓል፡፡

ሆኖም ሟቾች በደረሰባቸው ድብደባ፣ እንግልት፣ ያለ በቂ ምግብና ውሃ፣ ንጽህናቸው ባልተጠበቁ ቦታዎች ተይዘው በመቆየታቸው ለቲቪ እና አካኪ ለተባለ የቆዳ በሽታ በመጋለጣቸው በ2011 ሁለቱም ግለሰቦች ሕይወታቸው አልፏል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበባቸው ኪዳኔ ዘካሪያስ እና አባሪው ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው ክደው በመከራከራቸው፣ ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ ካሰማ በኋላ በበቂ ሁኔታ በማስረዳቱ ተከላከሉ ተብለዋል፡፡

ነገር ግን ኪዳኔ ዘካሪያስ ከዛሬ ነገ መከላከያ ምስክሮቼን አቀርባለሁ በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በማድረግ እና ክርክሩን በማዘግየት በመሃል ከእስር ማምለጡን ያመለከው ዐቃቤ ህግ፣ ተከሳሽ በሌለበት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እና በ1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንደተወሰነበት አሳውቋል፡፡

በተመሳሳይ ፍርድ ቤት በሊቢያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ስቃይ ሰበብ እንደሆነ የተነገረለት ተወልደ ጎይቶም ላይ የ18 ዓመት እስር ውሳኔ እንዳሳለፈበት መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img