አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 10፣ 2013 ― የመብት ተሟጋቹ ሲፒጄ በኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ በሚካሄደው ምርጫ ሰበብ ኢንተርኔት ሊቋረጥ ስለሚችል ጋዜጠኞች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ፖለቲካዊ ውጥረት ሲጋጋል ኢነተርኔት የማቋረጥ ከፍ ያለ ታሪክ ያላት አገር መሆኗን ያስታወሰው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ፣ ይህም ለጋዜጠኞች ሥራ ፈታኝ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጧል፡፡
ይህ በመሆኑም ጋዜጠኞች ድንገት ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ቢቋረጥ ብለው ማቀድ አንደሚኖርባቸው ያሳሰበ ሲሆን፣ ጋዜጠኞች በበይነ መረብ ያስቀመጧቸውን ሰነዶች በወረቀት እንዲይዙ፣ መረጃ ማከማቸዎችን ቀድመው እንዲያዘጋጁ፣ እንዲሁም ኢንተርኔት በሚቋረጥባቸው ወቅቶች አገልግሎቱን የሚያገኙባቸውን እንደ ኤምባሲ ያሉ አማራጮችን ለይተው እንዲይዙ መክሯል፡፡