Monday, September 23, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምርጫውን እንዳይታዘብ መከልከሉ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 10፣ 2013 ― የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ለመታዘብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ቦርዱ ጥያቄውን እንደማይቀበለው ገልጧል፡፡

በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ መታዘብ ከሥራዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ ጥያቄ ያቀረበው ኢሰመኮ፣ ተቀባይነት ያላገኘው በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው አካላት መካከል ባለመካተቱ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።

ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮቼ አገኘሁት ያለውን ደብዳቤ ጠቅሶ አንደዘገበው፣ ቦርዱ የተሻሻለውን የምርጫ ሕግ በመጥቀስ ‹‹ኢሰመኮ የታዛቢነት፣ የጋዜጠኝነት ወይም ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል ዕጩ ወኪል ስላልሆነ ቦርዱ የይለፍ ካርድ የሚሰጥበት የሕግ አግባብ ባለማግኘቱ ጥያቄውን ተቀብሎ ማስተናገድ›› እንዳልቻለ ገልጧል፡፡

ሰኔ 7፣ 2013 ተጽፎ የቦርዱ አባል በሆኑት በአቶ ውብሸት አየለ ጌጤ ተፈርሟል በተባለው በዚህ ደብዳቤ፣ የምርጫ አዋጁን አንቀፅ 123 በመጥቀስ ለተፈቀዳለቸው ሰዎች የይለፍ ካርድ እንደሚሰጥ እንደሚያብብራ ዘገባው አመልክቷል፡፡

ኢሰመኮ ለቦርዱ ሰብሳቢ በማግስቱ ሰኔ 08፣ 2013 የላከው ደብዳቤ ውሳኔው አግባብ አይደለም በማለት ለቦርዱ ሰብሳቢ አቤቱታውን አቅርቧል።

ይህም የተሻሻለውን የኮሚሽኑን አዋጅ በማንሳት፣ ለኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባር እና ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ምርጫን መታዘብ የሚል እንደሚገኝበት በመጥቀስ ያስረዳል።

ቦርዱ ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ ላይ የተሻሻለው የኮሚሽኑ አዋጅ በምርጫ ወቅት ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶችን አጠባበቅ በተመለከተ ክትትል እንዲያደርግ ስልጣን እንደሚሰጠው እንደሚረዳ ገለፆ፤ ነገር ግን ይህን የመታዘብ ሥራ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲገባ የሚያስችለው የይለፍ ካርድ ከሚሰጣቸው አካላት ውስጥ የምርጫ አዋጁ አያካትተውም ብሏል።

ይህ በዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የተፈረመው ባለ ሁለት ገፅ ደብዳቤ ከተጠቀሱት 10 ነጥቦች ውስጥ ሁለተኛው ‹‹ኮሚሽኑ ይህንን ተግባር እና ኃላፊነቱን የሚወጣው በምርጫ ጣቢያዎች ጭምር በመገኘት ነው‹‹ ሲል የሞገተ ሲሆን፣ ‹‹ለአብነትም የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆናቸውን ለመረጋገጥ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት የሚጣራ ነው›› ሲል ጠቅሷል።

አክሎም ዓለም አቀፍ የምርጫ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ እጅግ የተለመደ ነው ያለው ደብዳቤው፣ ይህም ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማትን ያሳተፈ ነው ይላል።

የኢሰመኮ የሕዝበ ግንኙነት ኃላፊ አሮን ማሾ በቦርዱ እና በኮሚሽኑ መካከል ንግግሮች እየተደረጉ መሆኑን አረጋግጠው፣ በደብዳቤዎቹ ላይ ግን አስተያየት ለመስጠት ተቆጥበዋል ነው የተባለው፡፡

በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img