አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 9፣ 2013 ― አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት ለመውጣት የቀራቸው ‹‹አንዳንድ ቴክኒካዊና የአፈጻጸም ጉዳዮች ናቸው›› ማለታቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አሶሺየትድ ፕሬስ ወታደሮቹ እንዲወጡ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ቁርጠኝነት እንዳለና ‹‹በኤርትራውያኑ በኩልም ሁሉ ነገር ግልጽ›› መሆኑን አመባሳደሩ ተናግረዋል ብሏል፡፡
አምባሳደሩ ይህን የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በጸጥታው ምክር ቤት ቀርበው ‹‹ግጭቱ እንዲቆም ተደርጎ የኤርትራ ወታደሮች ካልወጡ የ1977 ዐይነቱ የከፋ ረሃብ ተመልሶ ቢከሰት ማንም መደነቅ የለበትም›› ብለው ከተናገሩ በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት የተደገፈው በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሚመለከት ትንተና ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሎውኮክ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ አለ ብለው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ረሃብ ተከስቷል የሚለውን ዘገባ አስተባብሎ በተለይ በትግራይ ክልል ውስጥ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።
አሁን በቅርቡ ይወጣሉ የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች፣ በትግራይ ክልል የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው በተደጋጋሚ ሲከሰሱ የቆዩ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ወታደሮቹ እንዲወጡ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።