አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 9፣ 2013 ― አፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ስለተባሉ የመብት ጥሰቶችን በይፋ መመርመር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ምርመራ ነገ ሰኔ 10፣ 2013 በይፋ እንደሚጀምር የኮሚሽኑ መግለጫ ያመላክታል።
በዚሁ መሰረት በትግራይ ክልል መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እንደሚመረምር የገለጸወ ኮሚሽኑ፣ አስፈላጊ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላም የጎረቤት ሀገራትን ሁኔታ ለማየት እንደሚሞክር ነው የገለጸው።
ኮሚሽኑ ለሦስት ወራት ተቀምጦ ሁኔታውን እንደሚመረምር የገለጸ ሲሆን፤ የሶስት ወራት ጊዜውም ሊታደስ እንደሚችልም ነው የተገለጸው።
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን የመብት ጥሰቶችን የመመርመር ኃላፊነት እንዳለውም ነው ያመለከተው፡፡