Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከፊል ጊዜያዊ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ ነኝ አለች

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 8፣ 2013 ― ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ልታከናውን በተቃረበችበት ጊዜ አንዳንድ ሁኔታዎች ከተሟሉ ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከፊል ጊዜያዊ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

ከዚህ ቀደም ሱዳን ከሌላኛው የውሃው ተደራዳሪ ግብጽ ጋር ‹‹<ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይፈረም›› ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ አጥብቃ ስትቃወም በመቆየቷ አዲሱ የሱዳን አቋም እያነጋገረ እንደሚገኝ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ትላንት ካርቱም ውስጥ እንደተናገሩት ጊዜያዊ ስምምነቱ የሚፈረመው ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ ሬውተርስ ዘግቧል።

በዚህም መሠረት በቅድመ ሁኔታነት የቀረቡት ጉዳዮች በሐምሌ ወር ለማካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ሁለተኛ ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በኋላም ድርድሩ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ከተሰጠ፣ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት የተደረሰባቸው ሁሉም ጉዳዮች ላይ አገራቱ የመጨረሻ ፊርማቸውን ካኖሩ እና ድርድሮች የሚካሄዱበት ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ እንዲኖር የሚሉ ናቸው።

በተጨማሪም የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ አማራጭ ሐሳብ ባቀረቡበት በትላትናው መግለጫቸው ላይ አገራቸው የግድቡን ውዝግብ ለመፍታት ወታደራዊ ግጭትን ፈጽሞ እንደ አማራጭ እንደማታየው መናገራቸውን የሱዳን ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል። ከዚያ ይልቅ ሱዳን ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች የመፍትሔ መንገዶችን እንደምትጠቀም አመልክተዋል። በዚህም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት፣ በወዳጅ አገራትንና በሌሎች በሚመለከታቸው ወገኖች አማካይነት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ እንደምትሻ ገልጸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ለአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ኳታር የሚገኙት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አገራቸው ጥቅሟን ለማስከበር ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው የሐምሌ ወር ተከናውኖ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img