Friday, October 11, 2024
spot_img

ምርጫው ነገሮችን ከማሻሻል ይልቅ በአገሪቱ አለመተማመን የሚፈጥር መሆኑን አንድ ዓለም አቀፍ ምሁር ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 8፣ 2013 ― በኢትዮጵያ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት አገራዊ ምርጫ በአገሪቱ ነገሮችን ከማሻሻል ይልቅ አለመተማመን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን የኢንተርናሽናል ኢኒስቲትዩት ፎር ኤሌክቶራል ዴሞክራሲ አማካሪ እና ተንታኝ የሆኑት ዶክተር አደም አበበ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር አደም በበርሊን በሚታተመው ኢንተርናሽናል ፒሊቲክስ ኤንድ ሶሳይቲ ላይ ባስነበቡት መጣጥፍ በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችን የዳሰሱ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚታየውን ዘር ተኮር የእርስ በርስ ግድያ፣ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎችን መታሰር እና ሌሎችንም ጠቅሰዋል፡፡

ተንታኙ በመጣጥፋቸው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት የቀረውን ምርጫ አስመልክቶም የጻፉ ሲሆን፣ ምርጫ ምንም እንኳን ምርጫ የአንድን አገር ሽግግር ለማፋጠን ዐይነተኛ ሚና ቢኖረውም የአሁኑ የኢትዮጵያ ምርጫ ግን ዋንኛ የሚባሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተፎካካሪዎች እስር ቤት አጎሮ የሚደረግ ስለሆነ ሽግግሩን የማፋጠን ሂደቱ ላይ ጥላ እንዳጠላበት አስረድተዋል፡፡

ይኸው ጥላ እንዲገፈፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፖሊቲካዊ ውሳኔዎችን ሊያሳልፉ እንደሚገባ የጠቆሙት ዶክተር አደም፣ እነዚህ ውሳኔዎች በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን መፍታትን እንደሚያካትት አስፍረዋል፡፡

በተጨማሪም በትግራይ ክልል አለ ያሉትን አሳዛኝ ሁኔታ እንዲሁም የትግራይና የአማራ ክልሎችን የድንበር ችግሮችን ለመፍታት ፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ተንታኙ ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ የሚካሄደው ምርጫ ግን አገሪቱን ከችግሮችዋ ሊያወጣት እንደማይችልና ይበልጡኑ ወደ አለመተማመን የሚገፋ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በመጀመሪያ ዙር የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14፣ 2013 ሊካሄድ ቀጠሮ እንደተያዘለት ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img