አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 8፣ 2013 ― በሊቢያ ድንበር ሰዎችን ወደ አውሮፓ በሕገ ወጥ መንገድ አዘዋውራለሁ በሚል ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ስደተኞችን ሲያሰቃይ ነበር የተባለውና እጅግ አደገኛ እንደሆነ የሚነገርለት ተወልደ ጎይቶም ወይም በስፋት በሚታወቅበት ሥሙ ‹ወሊድ› ላይ ፍርድ ቤት የ18 ዓመት እስር እንደፈረደበት ተሰምቷል፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን አዘዋዋሪው ግለሰብ ስተደኞችን በማገት ከፍተኛ ገንዘብ ከማስከፈል ጀምሮ በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ እና ሌሎችም በስደተኞች ላይ ይፈጽማቸዋል በተባሉ አሰቃቂ የሚባሉ የግፍ ተግባራት በጥብቅ ሲፈለግ የነበረና ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር የዋለ ነው፡፡
ከ2006 እስከ 2010 ባለው ጊዜ አሰቃቀቂ ተግባራቱን ሲፈጽም ቆይቷል የተባለው ተወልደ ጎይቶም፣ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር በቁጥጥር ስር ሲውል አብሮት ይሠራ የነበረ ወንድሙ እና ኪዳኔ ዘካሪያስ ከሚባል ሌላ ተፈላጊ ኤርትራዊ እና አንዲት ሴት ጋር ባንድነት በአዲስ አበባ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡
የአደገኛው ሰው አዘዋዋሪ ተወልደ ጎይቶም በቁጥጥር ስር መዋል እና የፍርድ ሒደቱ የአውሮፓ ጋዜጦች እና የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ዘንድ በስፋት ሲወራለት የሰነበተ ጉዳይ ነበር፡፡