Sunday, September 22, 2024
spot_img

የቡድን ሰባት ሀገራት በትግራይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሰኔ 6፣ 2013 ― የበለጸጉት ቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

መሪዎቹ ለሶስት ቀናት ያካሄዱትን ስብሰባ ሲያጠናቀቁ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ባወጡት ባለ 70 ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ በትግራይ የቀጠለው ግጭት፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ መጋለጥን ጨምሮ እየተፈጠረ ያለው ግዙፍ ሰብዓዊ አደጋ አሳስቦናል ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የናጠጡ ሰባት የዓለም ሀገራት መሪዎች በእንግሊዝ ባደረጉት የፊት ለፊት ስብሰባ አንገብጋቢ ብለው ከመከሩባቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ፤ በትግራይ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ አንዱ ነው። የሀገራቱ መሪዎች ዛሬ ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ “ጠብ ጫሪነት በፍጥነት እንዲቆም፣ በሁሉም አካባቢዎች የእርዳታ ድርጅቶች ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲፈቀድላቸው እና የኤርትራ ወታደሮች በአፋጣኝ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።

የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች በዚሁ መግለጫቸው፤ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ያሏቸውን ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ አሰቃቂ ድርጊቶችን አውግዘዋል። መሪዎቹ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የተጀመረውን ምርመራም በጸጋ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።

የቡድን ሰባት አገራት መሪዎች ግን በዛሬው መግለጫቸው “ሁሉም ወገኖች ለቀውሱ ብቸኛ መፍትሔ የሆነውን ተዓማኒ የፖለቲካ ሒደት እንዲከተሉ” ጥሪ አቅርበዋል። መሪዎቹ “ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ እና የፖለቲካ መብቶች የሚከበሩበት” መጻኢ ጊዜ ሲባል የኢትዮጵያ መሪዎች ሊከተሉት የሚገባውን ሂደትም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

“የኢትዮጵያ መሪዎች ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት የሚፈጥር ሰፊ እና አካታች የፖለቲካ ሂደት እንዲከተሉ ጥሪ እናቀርባለን” ማለታቸውንም የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው።

የቡድን ሰባት ሀገራት ተብለው የሚጠሩት ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ናቸው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img