Wednesday, December 4, 2024
spot_img

መንግሥት የትግራይ ክልልን መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት በዚህ ሳምንት ይፋ ያደርጋል

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሰኔ 6፣ 2013 ― መንግሥት የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም ከለጋሽ አገሮችና አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር ያዘጋጀውን ፕሮጀክት፣ በዚህ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

ፕሮጀክቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ሀብት በማፈላለግና ሥራውን በማስተባበር፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና ሌሎች በርካታ አካላት ተካተውበት እንደተቀረፀ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት ይፋ እንደሚደረግ የተገለጸው ትግራይን መልሶ የመገንባትና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት፣ በደረሱ ውድመቶች ላይ ጥናት ከማካሄድ በተጨማሪ ከበርካታ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት የተደረገበት መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ይህ በዚህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሐሙስ ሰኔ 4፣ 2013 ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል ከግንቦት 2013 እስከ ታኅሳስ 2014 ድረስ ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት የሚውል 853 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ በተጠቀሱት ወራት ለሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልጋል ከተባለው አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ፣ የ502 ሚሊዮን ዶላር ክፍተት መፈጠሩን ገልጿል፡፡

በክልሉ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ ከሚፈጸመው ስርቆት በተጨማሪ ግጭት ለሥራቸው እንቅፋት መሆኑን ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ያልተጠበቁ ጥቃቶችና የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋል አዝማሚያዎች፣ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እንደሚሰነዘሩ አክሎ ገልጿል፡፡

የተመድ የሰብዓዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በክልሉ እየታየ ያለው ችግር በአፋጣኝ ካልተፈታ፣ በአሁኑ ጊዜ ያጋጠመው የምግብ እጥረት ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img