አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 5፣ 2013 ― የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አገራቸው እንደምትቃወም መናገራቸውን ዢንዋ ዘግቧል፡፡
የዜና ተቋሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዋንግ ይ ‹‹ሁለቱ አገራት የሚተባበሩ አጋሮች ናቸው››፣ እንዲሁም ‹‹ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና መረጋጋቷን የመጠበቅ መብት አላት›› ማለታቸውን አስነብቧል።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮቿን በዋነኛነት በራሷ ጥረት መፍታት አለባት። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ፍቃድ አክብሮ ድጋፍ መስጠት ነው ያለበት። ማዕቀብ መጣልም የለበትም›› ማለታቸውም ተዘግቧል።
በተጨማሪም የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ ‹‹ቻይና በትግራይ ክልል ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማርገብ እርዳታ ለመስጠት ፍቃደኛ ናት። የመጀመሪያው ዙር የምግብ እርዳታም ተልኳል›› መባሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንንም በትዊተር ገጻቸው ‹‹ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር ባደረግነው ፍሬያማ የስልክ ውይይት የአገር ውስጥ ጉዳዮቻችንን ያለ ጣልቃ ገብነት ስለመፍታት ተነጋግረናል›› ብለዋል።
ምዕራባውያኑ አገራት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን፣ ሕዝቡ ለረሃብ መጋለጡን፣ ሰብዓዊ እርዳታ በአግባቡ አለመድረሱን እና ሌሎችም ችግሮችን በመግለጽ የኢትዮጵያን መንግሥት መተቸት ከጀመሩ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡