Wednesday, October 9, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት መርጃ በትግራይ 33 ሺሕ ሕፃናት በረሃብ የመሞት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ገለጸ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 5፣ 2013 ― በትግራይ 33 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት በሞት አደጋ ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ሕፃናት መርጃ ድርጅት ወይም ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡

ይህንኑ በትላንትናው እለት የተናገሩት የዩኒሴፍ ቃለ አቀባይ ጄምስ ኤልደር በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው ሁኔታ አደገኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረትም ዩኒሴፍ እርዳታ የሌላቸው አካባቢዎች የእርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች ጥሪ አቅርቧል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ሐሙስ ዕለት የወጣውና የክልሉን ሁኔታ የገመገመው ሪፖርት በክልሉ ያለውን የምግብ አጥረት ሁኔታ በተመሳሳይ አደገኛ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡

በትግራይ ክልል ጦርነት ከተከሰተበት ከጥቅምት 24 ጀምሮ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውና ክልሉም በከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ መሆኑን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሠረትም ከ350 ሺሕ በላይ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ በሚባል ችግር ውስጥ ናቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ረሃብ አለ እየተባለ የሚወጣውን መረጃ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ከማስተባበሉም ባሻገር በክልሉ እርዳታ በበቂ እየተከፋፈለ ነው ብሏል።

የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጄምስ ኤልደር ግን ‹‹በአሁኑ ወቅት የዳሰሳ ጥናት ከተደረገባቸው 20 በመቶው ሕዝብ መካከል 350 ሺሕ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ላይ መሆናቸውን ማሳየቱ ይፋዊ በሆነ መልኩ ረሃብ አለ ብሎ ለማወጅ ከተቀመጠው በታች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሰዎች እየሞቱ በቃላት ባንጫወት ጥሩ ነው›› በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባይቀበለውም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክም በትግራይ ረሃብ ተከስቷል በማለት ከሰሞኑ ተናግረው ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img