Thursday, October 10, 2024
spot_img

የባይደን አስተዳደር ከምርጫ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 5፣ 2013 ― የኢትዮጵያን የወደፊት አካሔድ ለመወሰን እና የአገሪቱን ዴሞክራሲና ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት መንግሥት እና መላ ኢትዮጵያውያን ከምርጫ በኋላ ለሚካሔድ አካታች የፖለቲካ ብሔራዊ ውይይት ቁርጠኛ እንዲሆኑ አሜሪካ ጥሪ አቅርባለች፡፡

የአሜሪካ መንግሥትን አቋም የሚያንጸባርቀው መግለጫ የወጣው አንቶኒ ብሊንከን በሚመሩት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ነው። መግለጫው መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ አሉበት ያላቸውን ፈተናዎች ዘርዝሮ ሥጋቱን ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚመሩት የአሜሪካ አስተዳደር በቅድሚያ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለሠራተኞቹ ጥረቶች እውቅና ቢሰጥም፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሔድበት ከባቢ ‹‹አሳሳቢ›› መሆኑን አመልክቷል፡፡

በአገሪቱ አለ ያለውን ‹‹የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስር፣ የገለልተኛ ሚዲያ መዋከብ፣ የአካባቢያዊ እና ክልላዊ መንግሥታት ወገንተኝነት እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያ በብሔሮች እና በማህበረሰቦች መካከል የተቀሰቀሱ ግጭቶች ለነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንቅፋት ናቸው›› ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በመግለጫ ዘርዝሯል፡፡

መግለጫው ፖለቲከኞች እና የማኀበረሰብ መሪዎች ሁከትን እንዲያስወግዱ እና ሌሎችንም ከማነሳሳት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች እና የማህበረሰብ መሪዎች ቅሬታዎቻቸውን በድርድር እና በውይይት ሊፈቱ ይገባል የሚል ምክር ለግሷል፡፡

ለነፃ ሚዲያ እና ንቁ የሲቪክ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መሪዎች ድጋፍ እንዲሰጡ ያበረታታው የአሜሪካ መንግስት፤ ‹‹የዜጎችን ሐሳብን የመግለጽ፣ ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብቶች መንግስት እንዲያከብር እና የኢንተርኔት አገልግሎትን ከመዝጋት እና ኔትወርክን ከመገደብ እንዲቆጠብ›› ጥሪ አቅርቧል።

አክሎም ‹‹በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች በክልሎች እና ብሔሮች መካከል ያለው ልዩነት መካረር የአገሪቱን አንድነት እና የግዛት ሉዓላዊነት ያሰጋል›› ያለው የአሜሪካ መንግስት መግለጫ፣ ከምርጫው በኋላ መፍትሔ ሊፈለግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ‹‹ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እነዚህን ልዩነቶች ለመጋፈጥ ሁነኛ ወቅት›› መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img