Friday, November 22, 2024
spot_img

ፌስቡክ የኢትዮጵያን ምርጫ ተአማኒነት ለማረጋገጥ የሚሰራችው ስራዎች ላይ አዳዲስ የመቆጣጠሪያ መንገዶችን ይፋ ማድረጉን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 4፣ 2013 ― በመላው ዓለም በርካታ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ፌስቡክ በኢትዮጵያ በሁለት ዙር ከሚካሄድው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተገናኘ የምርጫውን ተአማኒነት ለማረጋገጥ የሚሰራችው ስራዎች ላይ አዳዲስ የመቆጣጠሪያ መንገዶችን ይፋ ማድረጉን ዛሬ በምሥራቅና አፍሪካ ቀንድ ቢሮዉ በኩል ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በሀገሪቱ በሚካሄደዉን ምርጫ በድምፅ አሰጣጡ ወቅትና ከዚያም በኋላ ሁከትን የሚቀሰቅሱ የጥላቻ ንግግሮችን እና ይዘቶችን ለመለየት እና ለማስወገድ ብሎም የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን ለመቀነስ የሚያግዙ ተግባራትን አንደሚከውን ነው ያመለከተው፡፡

ፌስቡክ በኢትዮጵያ የምርጫ ተአማኒነትን ለማገዝ ይረዳሉ በማለት ይፋ ካደረጋቸዉ ተግባራት መካከል የፌስቡክ የምርጫ ክወና ማዕከልን ስራ ማስጀመር አንዱ ሲሆን፣ ይህም ምርጫው በሚከናወንበት ወቅት በማዕከሉ ባለሙያዎችን በመመደብ የምርጫው ሂደት ላይ አንቅፋት ይፈጥራሉ ተብለዉ የሚለዩ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ አፋጣኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል አሰራር ነው፡፡

ይህ አሰራር ሀገርኛ ዕውቀትንና መረዳትን እንደመጠየቁ የተሳሳቱ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን፣ የምርጫ መረጃዎችን የሚከታተሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ቡድን ተዋቅሮ በስራ ላይ አንደሚገኙም ፌስቡክ ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪም የጥላቻ ንግግርን እና ሌሎች ጎጂ ይዘቶችን ለማቆጣጠር ፌስቡክ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብትን የሚጥሱ ይዘቶችን ሲያዩ ሪፖርት እንዲያደርጉና ሪፖረት ማድረጊያ መንገዶችን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል ቀለል ያደረገ ሲሆን ይህም ፌስቡክን ለሚያከናውነው ምርመራ ያግዘዋል ሲል መግላጫዉ አስፍሯል፡፡

በምርጫ ወቅት፣ በፊትና በኋላ ሊታዩ የሚችሉ የጥላቻ ንግግሮችን ወይም አመፅን እና ብጥብጥን የያዙ ሊሆኑ ይችላል የሚላቸውን የይዘት እና አስተያየቶች ስርጭትን በእጅጉ ለመቀነስ ፌስቡክ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ አንደሆነ የሚያስረዳዉ መግለጫዉ ባለሙያዎቹ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ የፌስቡክ ፖሊሲዎችን እንደሚጥስ ካረጋገጡ ይዘቱ ወዲያውeኑ ከድረ ገጹ ላይ አንደሚወገድ ይገልጻል።

በተጨማሪም የተሳሳተ መረጃ እና የሐሰት ዜናዎችን ለመዋጋት፤ የተሳሳተ አድራሻ፣ ጊዜ ያለፈበት ወይም ዐውዱን ያልጠበቀ ምስል ችግሮችን ስለመፍታት፤ የፖለቲካ ማስታወቂያዎችን ግልጽነት ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራትን ጭምር እየከወነ አንደሚገኝም ይፋ ማድረጉን የአዲስ ዘይቤ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ፌስቡክ በፈረንጆቹ ከመጋቢት 2020 እስከ መጋቢት 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ 87 ሺሕ የጥላቻ ንግግሮችን ማስወገዱን ያመለከተ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 89 በመቶ የሚሆኑት በተጠቃሚዎች ሪፖርት ከመደረጋቸው በፊት ተገኝተው እርምጃ አንደተወሰደባቸውም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img