አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 4፣ 2013 ― የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ወይም ዩኤስኤድ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ካላስቆሙ እና የኤርትራን ሠራዊትን ካላስወጡ በኢትዮጵያ የረሃብ ታሪክን በመድገም የሚታወሱ መሪ ይሆናሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሳማንታ ፓወር ይህን የተናገሩት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትላንት ትግራይ ክልልን በተመለከተ በቤኔ መረብ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡
በዚሁ ውይይት ላይ የተሳተፉት ሳማንታ ፓወርን ጨምሮ፣ የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ፣ የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይን እና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ከስብሰባቸው በኋላ በትግራይ የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ መተግበር አለባቸው ያሏቸውን አምስት ጥሪዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የተኩስ አቁም ጥሪ ቀዳሚው ነው።
በትግራይ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ብሎም የሲቪሎችን ጥቃት ለማስቀረት ተኩስ አቁም ይደረግ ሲል በአራት ባለሥልጣናት ተፈርሞ የወጣው ይህ መግለጫ ጠይቋል።
ባለሥልጣናቱ በሁለተኛ ደረጃ ያቀረቡት ጥሪ በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎችን እንዲያከብሩ የሚያሳስብ ሆኗለ።
ይህም የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ማስጠበቅን የሚጨምር ሲሆን ‹‹የተኩስ አቁም ተደረገም አልተደረገም ያለ ቅድመ ሁኔታ መተግበር አለበት›› ሲል መግለጫው አሳስቧል። የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ደኅንነት እንዲጠበቅም ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለውን የረሃብ አደጋ ለማስቀረት ሁሉም አካላት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚያስችል መንገድ እንዲፈጥሩ ተጠይቀዋል።
ሌላው የቀረበው ጥያቄ ከዚህ ቀደም በተገባው ቃል መሠረት የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ለቆ እንዲወጣ ለሁለቱ አገራት ጥሪ ቀርቧል።
በመግለጫው ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን የእርዳታ መጠን እንዲሳድግ እና የሰዎችን ሕይወት እንዲያድን ጥሪ ቀርቧል።